በቻይና ኤይድ ፕሮጀክት በኩል የተደረገ የወባ መድሃኒት ድጋፍ በቀጣይ ሳምንታት ወደ ሀገር ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በቻይና ኤይድ ፕሮጀክት በኩል የተደረገ የወባ መድሃኒት ድጋፍ በቀጣይ ሳምንታት ወደ ሀገር ይገባል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦ በቻይና ኤይድ ፕሮጀክት በኩል የተደረገ የወባ መድሃኒት ድጋፍ በቀጣይ ሳምንታት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከቻይና ኤምባሲ ሚኒስትር ካውንስል ዶክተር ያንግ ዪሃን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በቻይና ኤይድ ፕሮጀክት በኩል የተደረገ የወባ መድሃኒት ድጋፍ በቀጣይ ሳምንታት ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገባ በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ሚኒስትር ካውንስል ዶክተር ያንግ ዪሃን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና የቻይና ትብብር እና ወዳጅነት ከምንግዜውም በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመው ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የዶክትሬት ዲግሪ ስኮላርሺፕ ዕድል እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የቻይና ኤይድ ፕሮጀክት ያደረገው ድጋፍ የወባ መከላከል ጥረትን የሚደግፍ መሆኑን በመጥቀስ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
በውይይቱ 25ኛ ዙር የቻይና ሜዲካል ቡድን በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል የህክምና በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚመጣ የተገለጸ ሲሆን፤ ጤና ሚኒስቴር ለቡድኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ከቻይና የኮሌራ ቫክሲን ወደ ሀገር ለማስገባት በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን፤ የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ እና ባህላዊ ህክምናን ለማሳደግ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡