ቀጥታ፡

የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ለማሳካት ወሳኝ ሚና ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተገለጸ።         

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣የአፍሪካ ልማት ባንክ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን በመተባበር ያዘጋጁት በካፒታል ገበያ ላይ ትኩረት ያደረገ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ የፋይናንስ ተቋማት፣ዓለም አቀፍ ተቋማት፣የልማት አጋሮችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።   


 

በጉባኤው ላይ ካፒታል ገበያ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ፣በኢትዮጵያ ያለበት ደረጃ፣መልካም አጋጣሚዎችና ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችም ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።   

በኦዲት፣ታክስና የፋይናንስ ጉዳዮች አማካሪ የሆነው ዓለም አቀፍ ድርጅት የኬ ፒ ኤም ጂ የኢትዮጵያ ኃላፊ እና ቢዝነስ አማካሪ በርናርድ አሙካ፤ የካፒታል ገበያ ኃብትን ለማሰባሰብ ሁነኛና ተመራጭ መንገድ መሆኑን አንስተዋል።    

ኢትዮጵያም ወደዚህ ሥርዓት መግባቷ ትልቅ ውሳኔ መሆኑን ጠቅሰው ለመንግሥትም ሆነ ለግል ሴክተሮች መጠናከር አወንታዊ ሚና አለው ብለዋል።    

የውጭ ባለኃብትን በመሳብ ረገድም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመው ከካፒታል ገበያ በሰፊው ለመጠቀም ግን የበለጠ መሥራትን ይጠይቃል ሲሉ አስገንዝበዋል።   

በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ኃብት ለማሰባሰብ የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች ለማሳካት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

በምስራቅ አፍሪካ የኬ ፒ ኤም ጂ የማማከርና ስትራቴጂ ጉዳዮች ኃላፊ ጁሊየስ ጎንጋ፤ ኢትዮጵያ ወደ ካፒታል ገበያ ሽግግር ማድረጓ ወቅታዊና እና የዜጎችንም ኢንቨስትመንት ተሳትፎ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል። 

የካፒታል ገበያ ውጤታማ የሚሆነው በኢንቨስት አድራጊዎችም በመንግሥትም በኩል የሚያስፈልጉ ቅደመ ሁኔታዎች ሲሟሉ መሆኑንም ሊጤን እንደሚገባም ተናግረዋል።  

በኢንቨስትመንት መስክ የሚሳተፉ ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ላይ የጠራ ግንዛቤ በመያዝ መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።       

የካፒታል ገበያን በሚመለከት ከኢንቨስተሮችም ባለፈ ለሁሉም ዜጎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖር መስራትና በስፋት ማስተዋወቅም ይገባል ብለዋል።  

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የቴክኖሎጂ አማካሪ ዳንኤል ሳህሌ፤ የካፒታል ገበያው ትግበራን ለማሳለጥ ሕጎችን ከማውጣት ጀምሮ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው ብለዋል።     

በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች በኩል የመገበያያ ሲስተም መዘጋጀቱን ጠቁመው በብሄራዊ ባንክ በኩል ደግሞ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች የግምጃ ቤት ሰነድ መበልጸጉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም