የተማሪዎች የፈጠራ ሃሳብ ዳብሮና በልፅጎ ሥራ ላይ እንዲውል የተጠናከረ እገዛ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተማሪዎች የፈጠራ ሃሳብ ዳብሮና በልፅጎ ሥራ ላይ እንዲውል የተጠናከረ እገዛ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦የተማሪዎች የፈጠራ ሃሳብ ዳብሮና በልፅጎ ሥራ ላይ እንዲውል የተጠናከረ እገዛ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 9ኛው ሀገር አቀፍ የሳይንስና ኢንጂነሪንግ የፈጠራ ሥራዎች ውድድር አውደ ርዕይ ተጠናቋል፡፡
የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አሳታፊነት ዳይሬክተር ቀናቱ አንጋሳ (ዶ/ር)፤በሁነቱ በርካታ የፈጠራ ሃሳቦች ቀርበው የተወዳደሩበትና የልምድ ልውውጥ ጭምር የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።
የተማሪዎች የፈጠራ ሃሳብ ዳብሮና በልፅጎ ሥራ ላይ እንዲውል የተጠናከረ እገዛ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የስቴም ኢነርጂ ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ አቢዮት ላቀው፤ በፈጠራ፣በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ለተማሪዎች ውጤታማነት እገዛ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በውድድሩ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን ይዘው በመቅረብ ከተሸለሙት ተማሪዎች መካከል ከአሶሳ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት መናሂል አህመድ፣ ከወለጋ ዩንቨርሲቲ ሰኚ አየለ እና ከቀለም ስቲም ሴንተር እዮሲያስ ጎሹ፤ በውድድሩ በመሸለማቸው መደሰታቸውን ገልጸው፥ በቀጣይ ለተሻለ ስራ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በፈጠራ ውድድሩ ከመሸለምም ባለፈ ሰፊ እውቀትና ልምድ የተጋራንበት መልካም አጋጣሚ ነበር ሲሉም ገልጸዋል።
አውደ ርዕዩ የትምህርት ሚኒስቴር፣ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ከስቴም ፓወር ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅትና ከአጋሮች ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።