ቀጥታ፡

በመዲናዋ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ውጤታማ ናቸው-መሪየም ሳሊም

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና  በዓለም ባንክ  ትብብር በመዲናዋ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች  ውጤታማ ናቸው ሲሉ በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ፣ ኤርትራ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር መሪየም ሳሊም ገለፁ።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ዳይሬክተር መሪየም ሳሊም፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝታቸው  የአቃቂ የመንግስት ትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ ማዕከል፣ ብቃት ዛሬ ለነገ የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ ማዕከል፣የነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከልን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ኤርትራ፣ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር መሪየም ሳሊም በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ በዓለም ባንክ ድጋፍ በመዲናዋ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች  ውጤታማ ናቸው።

ይህን በዛሬው ዕለት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የመስክ ምልከታ በማድረግ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የምገባ መርኃ ግብር፣ ለወጣቶችና ሴቶች የተፈጠሩ የስራ እድሎችና የስራ ክህሎት ማዳበሪያ ፕሮግራሞች የሚደነቁ ናቸው ብለዋል።

በቀጣይ የዓለም ባንክ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የስራ እና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና  በዓለም ባንክ  ትብብር  በመዲናዋ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ውጤታማ ናቸው።

እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ 2016 እስከ 2020 ባሉት የመጀመሪያዉ ዙር በዓለም ባንክ ድጋፍ የተከነወኑ ስራዎች  ከ400 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል። 

በሁለተኛዉ ዙር ፕሮጀክትም አካታች በሆነ መልኩ በማስፋት የከተማ ድህነት ቅነሳ እና የስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረቱን ማድረጉን ጠቁመዋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና እንዳሉት ፤ በዓለም ባንክና በኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮግራሞች በከተማዋ ነዋሪዎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ ነው ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም