ብልጽግና የኢትዮጵያን የተረጅነት ታሪክ በመቀየር በሁሉም መስክ ስኬት እያስመዘገበ የሚገኝ ኅብረብሔራዊ ፓርቲ ነው-ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና የኢትዮጵያን የተረጅነት ታሪክ በመቀየር በሁሉም መስክ ስኬት እያስመዘገበ የሚገኝ ኅብረብሔራዊ ፓርቲ ነው-ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን የተረጂነት ታሪክ በመቀየር በሁሉም መስክ ስኬት እያስመዘገበ የሚገኝ ኅብረብሔራዊ ፓርቲ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትርና የፓርቲው የስራ አስፈፃሚ አባል ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
"የሀሳብ ልዕልና ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሀሳብ የጤና ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ አመራርና አባላት የ5ኛ ዓመት የፓርቲ የምስረታ ዓመት በዓልን አክብረዋል።
በዚሁ ጊዜ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር እና የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባል ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤ ብልጽግና የኢትዮጵያን የፖለቲካል-ኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ስብራት በመጠገን የመሪነት ሚናውን እየተወጣ የሚገኝ ፓርቲ ነው ብለዋል።
በፖለቲካው መስክም ከሀገር የተሰደዱና ታስረው የነበሩ ዜጎችን እንዲመለሱና ከእስር እንዲፈቱ በማድረግ በትብብር የሚያምን ፈር ቀዳጅ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ታሪክ በሚያስብል ደረጃ የተፎካካሪ ፓርቲ በመንግስት መዋቅር ውስጥ በማካተት ለጋራ ሀገር ግንባታ እንዲሰሩ ያደረገ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ መልኩም አንዱ ዋና፥ ሌላው ተመልካች የነበረበትን የፖለቲካ አውድ በመቀየር በአራቱም አቅጣጫ ሁሉንም የኢትዮጵያ ማንነቶች ሳያጓድል በፍትሐዊነት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢኮኖሚው መስክም የኢትዮጵያን የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ተመፅዋችነትን ታሪክ በማድረግ ለወጪ ንግድ ማቅረብ የተቻለበትን ታሪክ የሰራ ፓርቲ መሆኑን አስረድተዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም ወደተሟላ የትግበራ ምዕራፍ በማሸጋገር የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ በማድረግ የመሪነት ሚናውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
መመዘኛውን የሀገር ዕድገት ያደረገው የብልጽግና ፓርቲም የማይደፈሩ የሚመስሉና ቁርጠኝነትን የሚጠይቁ ስኬታማ የልማት ክንውኖችን እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የሚከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎችም ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ ከተሞችን በመፍጠር ለኢትዮጵያ ዕድገት የሚተጋ ፓርቲ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚና የጤና ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፤ የብልጽግና ፓርቲ የሰላም እጦትና የዴሞክራሲ ፍላጎት በኢትዮጵያ በተፋፋመበትና ጥላቻ በተንሰራፋበት ወቅት ዕውን የሆነ ፓርቲ ነው ብለዋል።
በዚህም መነሻነትም በኢትዮጵያ የተከማቹ ዕዳዎች ቢኖሩም ይህንኑ በማለፍ የተሻለ ዕድገትና ብልጽግናን እያረጋገጠ የሚገኝ ኅብረብሔራዊ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የሰነቀውን ራዕይ እውን ለማድረግ በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክብረ በዓሉም "ባለህልም መሪዎች፣ ትጉህ አባላት ለህዝባችን ስኬት፣ ሕብረ ብሔራዊ ፓርቲያችን ለሕብረ ብሔራዊ ሀገራችን !" የሚሉ መሪ ሃሳቦች ተንጸባርቀዋል።
የጤና ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት በፌዴራል ተቋማት የብልጽግና ፖርቲ ስር ከሚገኙ አደረጃጀት ውስጥ አንዱ መሆኑ ይታወቃል።