ለሀገራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለመሻት በሚደረገው ጥረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለመሻት በሚደረገው ጥረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦ለሀገራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለመሻት በሚደረገው ጥረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እገዛና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ጠየቁ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከ56 የመንግስት እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ምሁራንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ ብሔራዊ መግባባትና ለሀገረ-መንግስት ግንባታ ትልቅ መሠረት መጣልን ዓላማ አድርጎ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ኮሚሽኑ ቁልፍ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር በመስራት ላይ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እገዛና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ለሀገራዊ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለመሻት በሚደረገው ጥረት በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እገዛና ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፤ ኮሚሽኑ እስካሁን በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ህዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ ግብዓቶችን የማሰባሰብ ስራዎችን ጨምሮ ሌሎችንም ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ጉዞው በዘጠኝ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎች ባልተከናወነባቸው አከባቢዎች ማካሄድን ጨምሮ ሌሎች ስራዎችን ይሰራል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ደረጄ እንግዳ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት እገዛና ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸው ይህንም አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ጉቼ ጉሌ (ዶ/ር)፤ በአከባቢው ለተካሄዱት የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ መሳካት ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።