ቀጥታ፡

የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲን ለአርሶና አርብቶ አደሩ የማስገንዘብ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

አዳማ  ፤ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አዲስ የተቀረፀውን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲን ለአርሶና አርብቶ አደሩ የማስገንዘብ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት አስታወቀ ።

አዲሱን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲን ለመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ማስተዋወቂያ መድረክ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል ።

የኢትዮጵያ ግብርናና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ እንደገለፁት የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ውጤታማነት የሚረጋገጠው ህዝቡ በአግባቡ ዓላማውን መገንዘብ ሲችል ነው ።


 

የግብርና ስራችንን ለማሳለጥና የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ባለሙያዎች ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞችን ተገንዝበው የማስገንዘብ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።

በተለይ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሮች ዋና ዋና ሰብሎችን በኩታ ገጠም በማልማት ተመሳሳይ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂና ግብዓት እንዲሁም የኤክስቴንሽን አገልግሎት በመጠቀም እያመረቱ ይገኛሉ ብለዋል።

ነባሩ ፖሊሲ በምግብ ሰብል ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በሰብል፣ በእንስሳት ሀብት ምርታማነት፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል የምርታማነት አቅም መገንባት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል ።

በዚህም የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና የስነ ምግብ ስርዓትን እውን ከማድረግ ባለፈ የግብርና ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ግብ የተቀመጠበት የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መሆኑንም ጨምረው አብራርተዋል።

አሁን ላይ ከሰብል የስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ ሩዝ፣ በቆሎ እንዲሁም የእንስሳት ዝርያና ምርታማነት ማሻሻያ በተለይ በወተት ላሞችና ዶሮ እርባታ አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ የሰብል ምርትና ምርታማነት እያደገ መሆኑን ጠቁመዋል።

አዲሱ ፖሊሲ ይህንን አጠናክሮ በዘላቂነት የሚያስቀጥል በመሆኑ አርሶና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ሁሉም ህብረተሰብ እንዲረዳው የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ሙያዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያለመ መድረክ መሆኑን አመልክተዋል።

አዲስ የተቀረጸውን ፖሊሲና የዘርፉ ዕቅድ ለመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ለማስገንዘብ  መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል ።

በኢንስቲትዩቱ የፖሊሲና ምግብ ስርዓት ዳይሬክተር  አቶ ረታ ዋቅጋሪ በመድረኩ ላይ ባቀረቡት ጽሁፍ  አምና የፀደቀው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ 1994 የወጣውን ነባሩን ፖሊሲ የተካና አሁን ሀገሪቷ የደረሰችበትን የግብርና ዕድገት፣ ፍላጎትና ቀጣይ ግቦችን ለማሳካት ያለመ መሆኑን አመልክተዋል ።

በተለይ የቴክኖሎጂ አቅምን በስፋት መጠቀምና ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ፣ ዘመናዊ የመሬት አጠቃቀምና ምርታማነት ማሳደግ፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን መቋቋም የሚችል የግብርና ስርዓት መዘርጋት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል

መድረኩ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የፖሊሲውን ዓላማና ግብ በአግባቡ በመረዳት ለህዝቡ ግንዛቤ እንዲያስጨብጡ  በማሰብ  መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በመድረኩ ከመገናኛ ብዙሀን ተቋማት የተወጣጡ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም