ቀጥታ፡

የህብረት ስራ ማህበራት የገበያ ዋጋን በማረጋጋት ህብረተሰቡን በቅርበት ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ሊዘረጉ ይገባል

አሶሳ፤ ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦ የህብረት ስራ ማህበራት የገበያ ዋጋን በማረጋጋት ህብረተሰቡን በቅርበት ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ሊዘረጉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ "የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም ለሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ በአሶሳ ከተማ የንቅናቄ መድረክ አካሄዷል። 


 

የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሺሰማ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደገለፁት የህብረት ስራ ማህበራት በኢኮኖሚው ዘርፍ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ ነው። 

ሪፎርሙ የህብረት ስራ ማህበራት የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያዳብሩ እና ለህብረተሰቡ የብድር አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል እንደሆነም ጠቁመዋል። 

በ2016 በጀት ዓመት 516 ሺህ የሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከህብረት ስራ ማህበራት የብድር አቅርቦት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል። 

የህብረት ስራ ማህበራት የገበያ ዋጋን በማረጋጋት ህብረተሰቡን በቅርበት ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ሊዘረጉ እንደሚገባ አቶ ሺሰማ ተናግረዋል። 

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ28 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የህብረት ስራ ማህበራት አባል ናቸው ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ ማህበራቱ ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት ለሀገር ኢኮኖሚ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በህብረት ስራ ማህበር በኩል በማልማት የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል። 


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሬትና ህብረት ስራ ማደራጃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል ሀመድ በበኩላቸው በክልሉ ከ151 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የህብረት ስራ ማህበር አባል መሆናቸውን ጠቅሰው 405 ሚሊዮን የሚጠጋ  ካፒታል አፍርተዋል ብለዋል። 

ቢሮው የህብረት ስራ ማህበራቱ በኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ሪፎርሙን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ገልፀዋል። 

በመድረኩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የህብረት ስራ ማህበራት ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም