ኢንተርፕራይዞች ጠንካራ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት አበርክቷቸውን እንዲወጡ ይደረጋል-የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል - ኢዜአ አማርኛ
ኢንተርፕራይዞች ጠንካራ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት አበርክቷቸውን እንዲወጡ ይደረጋል-የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል
ድሬዳዋ፤ ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ጠንካራ አገር በቀል ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት ያላቸውን አበርክቶ እንዲወጡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አስታወቁ።
በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማትና በድሬዳዋ አስተዳደር ትብብር የተዘጋጀና በኢንተርፕራይዞችና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተገኙ ውጤቶች ላይ ያተኮረ የውይይትና የተሞክሮ ልውውጥ መድረክ ዛሬ በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በወቅቱ እንደገለጹት በአስር አመቱ አገር በቀል መሪ የኢኮኖሚ ሪፎርም ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን የማስፋፋት ስራ ተጠቃሽ ነው።
ዘርፎቹን በትኩረት በክላስተር መደገፍ ከድህነት የመውጣትና አንድ አገራዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብ የመገንባት ጉዞ የማሳካት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዘርፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች በክህሎት መር ዕውቀት የታገዘ የስራ ዕድል መፍጠሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ የወጣቶችን የቴክኖሎጂ ፈጠራን ወደ ስራ በማስገባት በኩል ወሳኝ በጎ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አመልክተዋል።
"የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በተቀናጀ መንገድ መደገፍና መምራት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በማስቀረትና ጥራት ያላቸውን ተወዳዳሪ ምርቶች ወደ ወጭ ለመላክ ያስችላል" ብለዋል።
በተጨማሪም የአገር ውስጥ ገበያን በማረጋጋትና ጠንካራ አገር በቀል ኢኮኖሚ በመገንባት ውስጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አብራርተዋል።
"እነዚህን ጅምር ተግባራት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በክላስተር መደገፍና መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ላይ ትኩረት መስጠት ይገባል" ብለዋል።
በዚህ ረገድ የድሬዳዋ አስተዳደር ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት እየተመዘገበ ያለው ውጤት በአርአያነት የሚጠቀስና በሌሎችም አካባቢዎች በተሞክሮነት መስፋፋት ያለበት መሆኑን አመልክተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው በአስተዳደሩ ለሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች 1ሺህ 200 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መሠረተ ልማት የተሟላላቸው 18 ሼዶችና የምርት ማሳያዎች በመገንባት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል ።
ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ ህጎችና አሠራሮችን በማስተካከል ምርትና ምርታማነት ከመጨመሩ ባሻገር በብዙ ሺ ለሚገመቱ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሪያ ምንጭ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
"እነዚህን አብነታዊ ጥረቶች በተቀናጀ መንገድ በማጠናከር የተጀመረውን አገራዊ የብልፅግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል" ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሴ (ዶ/ር) እንዲሁም የክልሎችና የከተማ መስተዳደሮች የኢንዱስትሪ እና የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊዎች በመድረኩ ተሳትፈዋል።
ተሳታፊዎቹ በድሬዳዋ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና በአስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንቅስቃሴዎች ላይ የመጡ ውጤቶችን በመስክ እየተመለከቱ ናቸው።