የአርሶ አደሮችን ጓሮና ኑሮ የለወጡ ቁጥሮች- “30-40-30” - ኢዜአ አማርኛ
የአርሶ አደሮችን ጓሮና ኑሮ የለወጡ ቁጥሮች- “30-40-30”

ለዛሬው ትውልድ ምግብ፣ ለመጪው ትውልድ ደግሞ ቅርስና ውርስ የሚሆን ሃብት የሰነቀው የ"30-40-30" ኢኒሼቲቭ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አርሶ አደሮች መንደር ተገኝቶ ስለ ’30-40-30’ አሃዞች አርሶ አደሮችን የሚጠይቅ ካለ የቁጥሮችን ትርጓሜና ስሌት በቅጡ መረዳት ይችላል።
እነዚህ ቁጥሮች በገጠራማው የክልሉ አካባቢዎች አባውራዎች ዘንድ ሕይወትም፣ አስተሳስብም ለውጠዋልና።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኅላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር የ’30-40-30’ ኢኒሼቲቭ የተጠነሰሰው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭን በመመርኮዝ ስለመሆኑ ያስታውሳሉ።
እነዚህ ቁጥሮች የተራ አሃዝ ስያሜ ሳይሆኑ በክልሉ ግብርና ወደ እመርታ ለማስፈንጠር የተቀየሱና ትውልድ ተሻጋሪ ዓላማ የሰነቁ ናቸው።
በ2014 ዓ.ም ጀምሮ እያንዳንዱ የክልሉ አርሶ አደር በሶስት ዓመታት ውስጥ ቢያንስ 100 የፍራፍሬ ዛፎች አልምቶ እንዲጠቀም መሰረት የሆኑም ናቸው።
በኢኒሼቲቩ የለሙ ፍራፍሬዎች የአርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል ያለሙ፣ 'ለዛሬው ትውልድ ምግብ፣ ለመጪው ትውልድ ደግሞ ቅርስና ውርስ ናቸው' ይላሉ።
የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ገቢ ምንጭ ማድረግ፣ ስራ ዕድል መፍጠር፣ ገበያ ማረጋጋት፣ ለኤክስፖርትና ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ማቅረብን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ዓላማዎችም አሏቸው።
በእያንዳንዱ አባውራ ጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲለማና ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል የተወጠነ ነው።
በዚህም በ'30-40-30'ን እያንዳንዱ አባወራ ጓሮውን እንደየአካባቢው ስነ-ምህዳር በሙዝ፣ በፓፓያ፣ በማንጎ፣ በቡና፣ በአቮካዶና በሌሎች ፍራፍሬ ችግኞች እንዲያለማ ተደርጓል።
'ያልተሄደበትን መንገድ በመሄዳችን በትግበራ ሂደቱ ፈተናዎች ነበሩ' የሚሉት ሃላፊው፤ ዛሬ ላይ ግን የ30-40-30 ኢኒሼቲቭ ፍሬ የቀመሱትን ሁሉ አስተሳስብ ለውጧል ይላሉ።
ኢኒሼቲቩ ባልተለመዱ አካባቢዎች የፍራፍሬ መንደሮች የተፈጠሩበት፣ የአርሶ አደሩ ኑሮና ጓሮ የተለወጠበት፣ የይቻላል አስተሳስብ የተፈጠረበት እንደሆነ ይናገራሉ።
በክልሉ የ30-40-30 ኢኒሼቲቭ በመተግበር ከሴፍቲኔት የተላቀቁና ኑሯቸውን ያሻሻሉ አረሶ አደሮች ለዚህ ምስክር ናቸው።
በስልጤ ዞን ውልባረግ ወረዳ ቶዴ ጠመዳ ነዋሪዎች አቶ ሀምዛ አሊዬ እና ባለቤታቸው አናጃ ኢሳ በሴፍትኔት ታቅፈው ሲረዱ የቆዩ ሲሆን በ30-40-30 ጓሯቸውን በቡና በማልማታቸው ዛሬ ገቢም፣ ምግብም ችለዋል።
በ500 የቡና ችግኝ ድጋፍ ጀምረው በየዓመቱ እያሳደጉ ዛሬ ላይ ቡናቸውን ለቅመው በመሸጥ ገቢ ማመንጨትና ነሯቸውን መደጎም ችለዋል።
ጓሯቸውን በማልማታቸውም ከሴፍትኔት መላቀቅ ብቻ ሳይሆን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ያላቸው ማህበራዊ ህይወት እንዲሻሻል ስለማድረጉም ገልጽው፤ በቀጣይነትም ሌሎች ፍራፍሬዎችን ለማልማት ተዘጋጅተዋል።
በውልባረግ ወረዳ ቢላዋንጃ ባቢሶ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ኢክማላ መሀመድ እና ልጃቸው መካ ኢክማላ ደግሞ አካባቢውን ያልተለመደ የሙዝ መንደር በማድረግ ኑሯቸውን እንዳሻሻሉ ይናገራሉ።
የ30-40-30 ንቅናቄ ሲጀመር በአካባቢው "ሙዝ አይለማም" በሚል የተሳሳተ እሳቤ ቅር እያላቸው ችግኞችን ወስደው የተከሉ ቢኖሩም በርካቶች በእምቢታ ጸንተው እንደነበር አስታውሰዋል።
በሂደት ውጤቱ ሲታይ ግን የልማቱ ተሳታፊዎች በዝተው በውጤትና የስኬት መንገድ ላይ መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
ከሳዑዲ አረቢያ የ10 ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ የተመለሰው ልጃቸው መካ ኢክማላ የስደት አስከፊነትን በማንሳት ተፈጥሮ በሰጠችን ጸጋ ሳንጠቀም በመቆየታችን ይቆጨናለ ይላል።
የ30-40-30 ንቅናቄም ወጣቶች ከስደት ይልቅ በጓሯቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ ዐይን የገለጠ እና የአስተሳሰብ ለውጥም ያመጣ ስለመሆኑ ይናገራል።
በሀድያ ዞን ሻሸጎ ወረዳ ዶዕሻ ጎላ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ይቴቦ ሽጉጤ፤ ኢኒሼቲቩን በመጠቀም ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር የሙዝ መንደር መስርተዋል።
የክላስተር ሙዝ መንደራቸው በሶስት ዓመታት ውስጥ የቤተሰባቸው ኑሮ እንዲሻሻል ያደረገና በቀላሉ ጸጋን ተጠቅሞ መለወጥ እንደሚቻል ያረጋገጠ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
የስልጤ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ሙበራ ከማል፤ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚል ንቅናቄ በርካቶች በተለይም በፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ልማት ተሳትፈው ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአካባቢ ያሉ ጸጋዎችን በመለየት የቡና፣ የሙዝና የአቮካዶ ክላስተር በማልማት ከፍጆታ አልፈው ለማዕከላዊ ገበያ እየቀረቡ ስለመሆኑም ይናገራሉ።
በሀድያ ዞን የሻሸጎ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ወንዱ መለሰ፤ የ30-40-30 የፍራፍሬ ልማት ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
በሙዝ ክላስተር አርሶ አደሮች በትብብር ሰርተው እንዲለወጡ ያስቻለ መሆኑን ገልጸው፤ አርሶ አደሮችም ውጤቱን በማየት ወደተጨማሪ ልማት እየገቡ ይገኛሉ ብለዋል።
የ30-40-30 ኢኒሼቲቩ 'ጥረት ካለ ስኬት እንዳለ ማሳየት የተቻለበት እና የግብርናው ዘርፍ አንኳር መሰሶዎችን ዕውን ለማድረግ ተስፋ ሰጭ ውጤት የተገኘበት መሆኑን አቶ ዑስማን ይገልጻሉ።
በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የግብዓት ፍላጎት በመጨመሩ ተደራሽነቱን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል።
የ30 40 30 የፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት አንድ አርሶ ወይም አርብቶ አደር በመጀመሪያ ዓመት 30፣ በሁለተኛው ዓመት 40 እና በሶስተኛ ዓመት 30 የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል ተጠቃሚ የሚሆንበት መርሃ ግብር መሆኑ ይታወቃል።