ኢመደበኛ ፍልሰትን በመከላከል ህጋዊነትን የተከተለ አካሄድን የሚያበረታታ ''ኮምፓስ'' የተሰኘ መረኃ-ግብር ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
ኢመደበኛ ፍልሰትን በመከላከል ህጋዊነትን የተከተለ አካሄድን የሚያበረታታ ''ኮምፓስ'' የተሰኘ መረኃ-ግብር ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦ ኢመደበኛ ፍልሰትን በመከላከል ህጋዊነትን የተከተለ አካሄድን የሚያበረታታ ''ኮምፓስ'' የተሰኘ መረኃ-ግብር ይፋ ሆነ።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅትና በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ ኤምባሲ ትብብር መረኃ ግብሩ ይፋ መደረጉም ታውቋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፤ ኢትዮጵያ በርካታ መደበኛ ያልሆኑ ፍልሰተኞች መተላለፊያና መዳረሻ ስለመሆኗ አንስተዋል።
በመሆኑም ችግሩን ለመከላከልና በዘላቂነት መፍትሄ ለመሻት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በዛሬው እለት ይፋ የተደረገው ''ኮምፓስ'' የተሰኘው መረኃ-ግብርም ኢመደበኛ ፍልሰትን በመከላከል ህጋዊነትን የተከተለ አካሄድን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
የኮምፓስ መርሃ- ግብር የመጀመሪያ ምእራፍ ሲተገበር እንደነበር አስታውሰው አሁን ይፋ የተደረገው ሁለተኛው ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ክርስቲን ፒሬኔ፤ የፍልሰተኞች ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ችግር መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር ለመከላከል የጋራ ጥረትና መፍትሄ የሚሻ መሆኑን ገልጸው በዚህ ረገድ የኔዘርላንድ መንግስት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በአብሮነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቱ ዋኔ፤ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች በዓለም ላይ የኢ-መደበኛ ፍልሰት እየተባባሰ መምጣቱን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ችግር መኖሩን ጠቅሰው ድርጅቱ ከመንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አንስተው የኮምፓስ መረኃ-ግብር ይፋ መደረጉም የዚሁ ጥረት አካል ነው ብለዋል።