ቀጥታ፡

በክልሉ ከአርሶ አደሩ የተሰበሰቡና የአካባቢውን ስነ ምህዳር የተላመዱ ከ40 በላይ ዋና ዋና የሰብል ዝርያዎች እየተባዙ ነው

መቀሌ፤ ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፡-በትግራይ ክልል ከአርሶ አደር እጅ የተሰበሰቡና የአካባቢውን ስነ ምህዳር የተላመዱ ከ40 በላይ ዋና ዋና የሰብል ዝርያዎች እየተባዙ መሆናቸውን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የትግራይ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ምርጥ ዘርና የእርሻ  የቴክኖሎጂ በማፍለቅ፣ በማባዛትና በማስተዋወቅ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል። 

በጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉ እርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ተክላይ አበበ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ኢንስቲትዩቱ የክልሉን ምርታማነት የሚያሳድጉ፣ ስነ ምህዳሩን የተላመዱና በፍጥነት የሚደርሱ የአዝርዕት ዓይነቶችን እያባዛ ነው። 


 

''በ2016/17 የምርት ዘመን ዋና ትኩረታችን የነበረው የቀጣይ ምርት ዘመን የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረትን ለማቃለል የሚያስችሉ የምርምር ስራዎችን ማከናወን ነበር'' ብለዋል ። 

በአሁኑ ወቅት እየተባዙ ያሉት የምርጥ ዘር ዝርያዎች በሄክታር የተሻለ ምርት የሚሰጡ ሲሆን፤ ስንዴ ከአንድ ሄክታር 50 ኩንታል፣ ጤፍ እስከ 25 ኩንታል እንዲሁም በቆሎ እስከ 60 ኩንታል ምርት ሊሰጡ እንደሚችሉም ለአብነት አንስተዋል። 

እነዚህ ዝርያዎች በክልሉ በሚገኙ የምርምር ማዕከላት በ947 ሄክታር መሬት ላይ እየተባዙ መሆናቸውንም ዶክተር ተክላይ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ከአርሶ አደር እጅ የተሰበሰቡና በኢንስቲትዩቱ የነበሩ የአካባቢውን ስነ ምህዳር የተላመዱ ከ40 በላይ ዋና ዋና የሰብል ዝርያዎች እየተባዙ መሆናቸውን ገልፀዋል። 

በክልሉ ያለውን የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ለማቃለል ኢንስቲትዩቱ ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ በክልሉ ካሉ  የምርምር ማዕከላት እና ከሞዴል አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑን ዶክተር ተክላይ ተናግረዋል። 

በተለይ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተለያዩ ድጋፎችን እንዳደረገም ምክትል ዳይሬክተሩ አመልክተዋል። 

በቀጣይም ከኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ጋር በመተባበር ምርጥ ዘር ከማባዛትና ከማላመድ በተጨማሪ በእንስሳት ሃብት፣ በተፈጥሮ ጥበቃና በግብርና ሜካናይዜሽን ረገድ እየተካሄዱ የሚገኙ የምርምር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ዶክተር ተክላይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም