በከተማው በዶሮና በወተት ላሞች እርባታና በወተት ተዋጽኦ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ

አክሱም ፤ ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦በአክሱም ከተማ በዶሮና በወተት ላሞች እርባታና በወተት ተዋጽኦ የሥራ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ነዋሪዎች ውጤታማ በመሆን ተጠቃሚነታቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን አስታወቁ።

በከተማ ግብርና በወተት ላሞች እርባታና በወተት ተዋጽኦ ሽያጭ ላይ ከተሰማሩ የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሺሻይ ካሳሁን አንዱ ናቸው። 

ሥራቸውን ሲጀምሩ ሶስት የወተት ላሞችን በማርባት መሆኑን ገልፀው፤ አሁን የ15 የወተት ላሞች ባለቤት እንደሆኑ ተናግረዋል። 

በየቀኑም ከ100 ሊትር በላይ የወተት ምርትና ተዋጽኦ ለተጠቃሚዎች እንደሚያቀርቡ ጠቁመው፤ ለሶስት ስራ አጥ ወጣቶችም የስራ እድል መፍጠራቸውን አመልክተዋል ።

በከተማው ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ የመኖርያ ቤት ማፍራት መቻላቸውንም ገልጸዋል። 

አምስት ልጆቻቸውን በተገቢው መንገድ እያስተዳደሩና እያስተማሩ መሆኑን የገለፁት ግለሰቡ፤ ከዕርባታ ጋር ተያይዞም ሆነ ለመጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲሁም ለመስኖ ልማት የሚውሉ ሁለት የውሃ ጉድጓዶችን አስቆፍረው እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረዋል። 

የከተማው አስተዳደር በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በገበያ ትስስርና በብድር አቅርቦት ረገድ ድጋፍ ካመቻቸላቸው የተሻለ ሥራ ለመስራት ዝግጁ እንደሆኑም ነው አቶ ሺሻይ ያረጋገጡት። 

ወጣ አበበ አለምብርሃን በጋዜጠኝነት በመጀመርያ ዲግሪ ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ ቢመረቅም ተቀጥሮ መስራትን ሳይጠብቅ ከብድርና ቁጠባ ተቋም 100 ሺህ ብር ብድር ወስዶ በአንዲት የወተት ላም ስራ መጀመሩን ገልጿል። 

ከአንዲት የወተት ላም ተነስቶ አምስት የወተት ላሞች እንዳሉት ገልፆ፤ በአሁኑ ወቅት ከሁለት የሚታለቡ ላሞች በቀን 23 ሊትር ወተት ለተጠቃሚ በማቅረብ የቀን ገቢውን ማሳደግ መቻሉን ተናግሯል። 

 

በአንዲት የወተት ላም ስራ የጀመሩት ወይዘሮ ለታይ ሐጎስ በበኩላቸው፤ አምስት የውጭ ዝርያ ያላቸው የወተት ላሞች ባለቤት መሆን መቻላቸውን ገልፀዋል። 

"ስራ ከመጀመሬ በፊት በከተማው አስተዳደር ስልጠናና የከተማ ቦታ ተመቻችቶልኝ ነበር" ያሉት ወይዘሮ ለታይ፤ በየቀኑ 30 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ ገቢያቸው ከፍ ማለቱን ተናግረዋል። 

ያለምንም የኢኮኖሚ ችግር ቤተሰቦቻቸውን እያስተዳደሩ ከመሆናቸውም በላይ የዘመናዊ መኖርያ ቤት ባለቤት ለመሆን መብቃታቸውን አመልክተው፤ በ100 ሺህ ብር ወጪ  የውሃ ጉድጓድ ማስቆፈራቸውንም እንዲሁ። 

በከተማው ስልጠና እና የመስርያ ቦታ ተመቻችቶላቸው በዶሮ እርባታ ከተሰማሩ ወጣቶች መካከል ወጣት ብርሃን ገብረ ሚካኤል አንዷ ናት። 

ሥራዋን ለመጀመር ከብድርና ቁጠባ ተቋም 20 ሺ መበደሯዋን ያወሳችው ወጣቷዋ፤ ከመቀለ ኢትዮ-ችክን ጫጩቶችና ቀለብ በማምጣትም 25 ቀናት ሲሆናቸው በሽያጭ ለተጠቃሚዎች እንደምታቀርብ ገልጻለች። 

በአሁኑ ወቅት 1 ሺህ 500 ጫጩቶችን በማሳደግ ላይ እንደምትገኝ የገለጸችው ወጣትዋ፤ ካፒታሏም 120 ሺህ ብር መድረሱንና ስራውም አዋጪ በመሆኑ አጠናክራ እንደምትቀጥል ተናግሯል። 

በዚሁ የዶሮ እርባታ ሥራ አራት ወንድሞቿን በሚገባ እንደምታስተዳድር ገልፃለች። 

በከተማው አራት ወጣቶች አንድ ላይ ሃፍታይ በሚል ስያሜ ማህበር አቋቁመው በአነስተኛ ካፒታል ሥራ መጀመራቸውን የሚናገረው የማህበሩ አስተባባሪ ወጣት ግርማይ አጽባሃ፤ በየቀኑ 160 እንቁላሎችን ለገበያ እንደሚያቀርቡ ተናግሯል። 

መንግስት ብድር እንዲያመቻችላቸው የጠየቀው ወጣት ግርማይ፤ "የእንስሳት ህክምና ባለሙያዎች ሊደግፉን ይገባል" ብሏል።

በከተማዋ ከቤተሰብ ባገኘው ብድር የዶሮ እርባታ የጀመረውና ከሁለት ሺህ በላይ የስጋ ዶሮ ጫጩቶችን በማሳደግ ላይ ያለው ወጣት አብርሃ ገብረ ህይወት በበኩሉ፤ "ስራው አዋጪ ነው" ብሏል። 

የከተማው አስተዳደርም ስልጠናና የሥራ ቦታ በማመቻቸት ድጋፍ እንዳደረገለት በመጠቆም፤ ሥራውን ከዚህ በላይ  ለማስፋት ግን ብድር እንደሚያስፈልገው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም