ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከብራዚል ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የማሳደግ ፍላጎት አላት - አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከብራዚል ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የማሸጋገር ፍላጎት እንዳላት በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ገለጹ።

አምባሳደር ልዑልሰገድ ለብራዚል ፕሬዝዳንት ሊዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ የሹመት ደብዳቤያቸውን አቅርበዋል።

ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በብራዚል እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን በመግለጽ በአጋርነት ለመስራትና ግንኙነቱን ለማሳደግ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ ዘርፍ፣በተለይም በግብርና የብራዚልን እና የኢትዮጵያን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸውም አመልክተዋል።

አምባሳደር ልዑልሰገድ፣ በኢትዮጵያና በብራዚል መካከል ያለውን የረዥም ጊዜ ታሪካዊ ወዳጅነት ወደ ላቀ የስትራቴጂክ አጋርነት ለማሸጋገር የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን ለፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።

የብራዚል ኩባንያዎች እና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም