ቀጥታ፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለምክክሩ ስኬታማነት እያከናወኑ ያለውን በጎ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ህዳር 6/2017(ኢዜአ)፦ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለምክክሩ ስኬታማነት እያከናወኑ ያለውን በጎ ሚና አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማህበረሰብ ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

በውይይቱም ከ56 የመንግስት እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኮሚሽኑ ብሔራዊ መግባባትና ለሀገረ-መንግስት ግንባታ ትልቅ መሠረት መጣልን ዓላማ አድርጎ እየሰራ ይገኛል ።

ኮሚሽኑ መግባባት ላይ ባልተደረሰባቸው ቁልፍ አገራዊ ጉዳዮች መግባባት ላይ ለመድረስ ወደ ስራ ገብቶ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

እስካሁን የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንደሆኑና የባለድርሻ አካላት ሚናም ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመው፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዚሁ አካል እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ምሁራን ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ እንዲመጣ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።


 

ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ጉዞው በተለያዩ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻልና መተማመን የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት እንዲፈጠር እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ለምክክሩ ስኬታማነት ሲሰራ የነበረውን ሥራዎች እስከመጨረሻው ድረስ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኮሚሽኑ እስካሁን በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ህዝባዊ ውይይቶችን በማድረግ ግብዓቶችን የማሰባሰብ ስራዎችን ጨምሮ ሌሎችንም ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም የተሳታፊ ልየታ ስራዎችን በማከናወን የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም ገልጸዋል።

በቀጣይ ጊዜያትም የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎች ባልተከናወነባቸው አከባቢዎች ማካሄድን ጨምሮ ሌሎች ስራዎችን እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም