የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2017(ኢዜአ)፦ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ጥሪ አቀረቡ።
የቻይና አፍሪካ (ኢትዮጵያ) የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መግባቷ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን መፍጠሩን ተናግረዋል።
ከዚህብ ባለፈ ለባለሀብቶች ምቹ የአሰራርና የህግ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን ገልጸው፥ አዳዲስ ዘርፎችም ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጋቸውን አብራርተዋል።
የካፒታል ገበያ፣ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት ማድረግ እንዲሁም ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ተፈቅደው የነበሩትን የንግድ ዘርፎች ለውጭ ኢንቨስተሮች መከፈታቸው ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የሰጠችው ትኩረት በቀጣናው የትብብር ማዕከልና ተመራጭ መዳረሻ እንድትሆን እያደረጋት መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የቻይና ባለሃብቶች በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም በግብርናው፣ በማዕድን፣ በዲጅታል እና በማምረቻው ዘርፍ ኢንቨስት በማድረግ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያና ቻይና ያላቸውን ጠንካራና ዘርፈ ብዙ የትብብር መስኮች አንስተዋል።
ጉባኤው የሁለቱን አገራት እንዲሁም በቻይና እና አፍሪካ መካከል ያለውን የምጣኔ ሃብትና የንግድ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረምና በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ያላት የምጣኔ ሃብት ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረጓን አስገንዝበዋል።
ሁለቱ አገራት በመሰረተ ልማት፣ ኢንዱስትሪያላይዜሽን፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና አቅም ግንባታ ጠንካራ ትብብር እንዳላቸውና በቻይና ባለሃብቶች የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ማስገኘታቸውን አስረድተዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ቻይና ለአፍሪካ ልማት ለምታደርጋቸው ትብብሮች ኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር ናት።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቺን ሃዪ (Chen Hai) በበኩላቸው ጉባኤው ቻይና ከኢትዮጵያና አፍሪካ ጋር ያላትን የንግድና ምጣኔ ሃብት ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክር ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ከጂያንሱ ግዛት ጋር በመሰረተ ልማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ያላት ትብብር እያደገ መምጣቱን ገልጸው በአሁኑ ወቅት 76 ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
የቻይናዋ ጂያንሱ ግዛት ዋና ገዥ ሹ ኩሊን ግዛቷ ትልቅ የምጣኔ ሃብትና ኢንቨስትመንት አቅም እንዳላት አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የጂያንሱ ግዛት ንግድና ኢንቨስትመንት ጠንካራ አጋር ስትሆን በአሁኑ ወቅትም የግዛቷ በርካታ ባለሃብቶች በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች በኢትዮጵያ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ ጋር በግብርና፣ በታዳሽ ኃይል፣ መሰረተ ልማት፣ ኢንዱስትሪና ሌሎች የትብብር መስኮች ጠንካራ አጋርነት ለመፍጠር እንሰራለን ነው ያሉት።
ጉባኤው በቻይና እና አፍሪካ መካከል ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክር የገለጹት ደግሞ የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ አካባቢ ከፍተኛ አማካሪ ሊአላ ሎኮሳንግ(ዶ/ር) ናቸው።
በአህጉሪቱ የመሰረተ ልማት፣ ግብርና፣ ንግድ፣ የግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፎችን ጨምሮ ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉ ብለዋል።
በቻይና አፍሪካ (ኢትዮጵያ) የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮችና ማበረታቻዎች ላይ ገለጻ ተደርጓል።