ቀጥታ፡

የ2017 ታላቁ ሩጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደህንነት አካላት ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ ገብተዋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2017(ኢዜአ)፦ የ2017 ታላቁ ሩጫ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታወቁ፡፡

የፀጥታና ደህንነት አካላት ዛሬ ባደረጉት ውይይት በየዓመቱ በአዲስ አበባ ከሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው ታላቁ ሩጫ ለ24ኛ ጊዜ ሕዳር 8 ቀን 2017 ይካሄዳል፡፡

በታላቁ ሩጫ 50 ሺህ ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት ሲሆን መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ በማድረግ እንደሚካሄድ ጠቁመው ውድድሩ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ከመገንባቱ ባለፈ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዕድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ዓላማው እንዲሳካ መላው የመዲናዋ ነዋሪ የዜግነት ኃላፊነቱን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኅብረተሰቡ እስካሁን በከተማዋ በድምቀት የተከበሩ በዓላትና የተከናወኑ ሁነቶች በሰላም እንዲጠናቀቁ ትብብር እንዳደረገው ሁሉ ይህ ታላቅ ስፖርታዊ ውድድርም በሰላም እንዲካሄድ ከፀጥታና ደኅንነት አካላት ጎን በመሆን የፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ሲመለከት የፀጥታና ደኅንነት አካላት ጥቆማ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

ለዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ያበለፀገውን የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን(EFPApp) ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመጠቀም በፍጥነት ጥቆማ በመስጠት ወይም መረጃውን በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታና ደኅንነት አካላት በአካል በማድረስ የድርሻውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም