ቀጥታ፡

በአክሲዮን ሽያጭ እና ባለቤትነት ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2017(ኢዜአ)፦ በካፒታል ገበያ ዓለም አቀፍ ጉባዔ በአክሲዮን ሽያጭ እና ባለቤትነት የተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።

የካፒታል ገበያ ዓለም አቀፍ ጉባዔ “ዘላቂነት ያለው መንገድን ማበጀት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባዔው የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች፣ የልማት አጋሮች እና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ተሳታፊ ሆነዋል።

ጉባዔውን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) ጋር በመሆን አዘጋጅተውታል።


 

ጉባዔው በካፒታል ገበያ እና በኢንቨስትመንት ላይ የተሻለ አቅም ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የካፒታል ገበያ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ያለው ቁልፍ ሚና የተመለከቱ ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

የካፒታል ገበያ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ፣ የካፒታል ገበያ የቁጥጥር አቅም ማጎልበት፣ ዘላቂ የፋይናንስ ስርዓት፣ ኢኖቬሽን እና የፋይናንስ ቴክኖሎጂ(ፊን ቴክ) ሌሎች የመወያያ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።

በጉባዔው መክፈቻ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ እድሎችና ተግዳሮቶች ላይ የፓናል ውይይት ተደርጓል።

በጉባዔው የሁለተኛ ቀን ውሎ የአክሲዮን ሽያጭና ባለቤትነት እና የካፒታል ገበያ ትስስር የተመለከተ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የካፒታል ገበያ ዓለም አቀፍ ጉባዔ እስከ ነገ እንደሚቆይም ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም