በህብረት ስራ ማህበራት የተደራጁ ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን እያጎለበቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በህብረት ስራ ማህበራት የተደራጁ ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን እያጎለበቱ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2017(ኢዜአ)፦በህብረት ስራ ማህበራት የተደራጁ ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ የአመራርና የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን እያጎለበቱ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን የሴቶችና ማህበራዊ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ሀመልማል ክብሬ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ በህብረት ስራ ማህበራት ከተደራጁ ከ26 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ውስጥ ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
ሴቶች የሚያጋጥማቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በመቋቋም በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅተው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን ብሎም አገራቸውን መቀየር እንደሚችሉ በተግባር አስመስክረዋል ነው ያሉት።
በተለያዩ የስራ መስኮች የተደራጁ ሴቶች በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በብድር አወሳሰድና አመላለስ የተሻለ አፈጻጸም እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
በተለይም የአርብቶ አደር አካባቢ ሴቶች በቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ላይ ያላቸው ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ነው ያነሱት።
በህብረት ስራ ማህበራት የተደራጁ ሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ የአመራርና የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸውን እያጎለበቱ መሆኑንም አመልክተዋል።
በቀጣይም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት መስራት ይገባል ነው ያሉት።
በፋይናንስና ቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ ሴቶች የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮት ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በዚህ ጉዳይ ላይ በቅንጅትና በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።