ቀጥታ፡

በክልሉ የከተማ ልማትን ለማቀላጠፍ በሃብት መሰብሰብና በግብዓት አቅርቦት ላይ ያተኮረ ተግባር እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

ባህር ዳር  ህዳር 5/2017 (ኢዜአ)፡-  በአማራ ክልል ከተሞች  የኢንቨስትመንት፣ የኢንዱስትሪና መሰረተ ልማትን ለማቀላጠፍ በሃብት መሰብሰብና በግብዓት አቅርቦት ላይ ያተኮረ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ገለጹ።

የከተማ ልማት ክላስተር ተቋማት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርትና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ዛሬ በባህርዳር   ውይይት   ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ በሚገኙ ከተሞች የኢንቨስትመንትና መሰረተ ልማት ተግባራትን ለማዘመን እየተሰራ ነው።

በዚህም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች በማጠናከር፣ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋትና የስራ እድል በመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

 በተጨማሪም የኮሪደር ልማት ፣ የስማርት ሲቲና ሌሎች የልማት ተግባራትን በማቀላጠፍ ከተሞችን ዘመናዊና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም አዳዲስ ስልቶችን በመጠቀም የገንዘብ፣ የቁሳቁስ፣ የቴክኖሎጂና ሌሎች ግብዓቶችን ለማሟላት በሩብ ዓመቱ የተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት ማስገኘታቸውን አስረድተዋል።

ካለፉት ዓመታት በተለየ ዘንድሮ የመንግስት ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎትና በሚያቀርቡት ምርት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲሰበስቡ የተቀመጠው አቅጣጫ ውጤት እያስገኘ መሆኑን አብራርተዋል። 

ይህም የተቋማትን ዝግጁነት በማሳደግ የሚካሄዱ የልማት ስራዎችን በውጤታማነት ለመፈጸም የሚያስችል በመሆኑ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የከተማ ዘርፍ ስራዎች የተቋማትን ትብብርና ቅንጅት የሚጠይቁ  መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥን ማቀላጠፍ፣ የኑሮ ውድነትን ማቃለል፣ የስራ እድል ፈጠራና ህገ ወጥ ተግባራትን ማስወገድ ከዋና ዋና ተግባራቱ መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ ጠቁመዋል። 

እነዚህን ተግባራት ባለፈው ሩብ የበጀት ዓመት በመፈጸም በኩል በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ ማከናወን በመቻሉ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አስረድተዋል። 

የከንቲባና የስራ አስኪያጅ ችሎትን በማቋቋም የመልካም አስተዳደር ችግርን ማቀለል መቻሉን ጠቁመው፤ "የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ"ም ለምርታማነት እድገት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን  አመልክተዋል።

 የኑሮ ውድነት ለማቃለልም አምራች ኢንዱስትሪዎችንና የሸማቾች ማህበራትን በማስተሳሰር የተከናወነው ስራ ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

በሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች፣ የመሰረተ ልማትና ሌሎችም የግንባታ  ዘርፎች የስራ አጥነት ችግር ለማቃለል ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

በመድረኩም 16 የሚሆኑ የክልል ቢሮዎችና የተጠሪ ተቋማት አመራር አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም