የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል - አፈ ጉባኤ ፀሐይ ወራሳ - ኢዜአ አማርኛ
የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል - አፈ ጉባኤ ፀሐይ ወራሳ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፀሐይ ወራሳ ገለጹ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፀሐይ ወራሳ እና የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አዳማ ትምጳዬ በክልሉ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፀሐይ ወራሳ እንዳሉት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በርካታ ትሩፋቶች የተገኙበት ነው።
በዓሉ የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጠናከር የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እንዲፋጠን ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያ ከፍ የምትልበት በዓል መሆኑን ጠቁመዋል።
ክልሉ በዓሉን ለማስተናገድ ኃላፊነት ከወሰደበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል።
በዓሉ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ በሆነው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መከበሩ ልዩ ትርጉም እንዳለው እና ክልሉን ለማስተዋወቅ ምቹ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት የሚገናኙበት እና እሴቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት፤ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ሁነቶች እንደሚከበር አመላክተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አዳማ ትምጳዬ በዓሉን በድምቀት ለማክበር በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ እና በአመራር ትኩረት ተሰጥቶት የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
ክልሉ በህገ-መንግሥታዊ መንገድ በህዝቡ ሙሉ ፍላጎት መመስረቱን ገልጸው፤ በተመሰረተበት ዓመት የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለማክበር እድል ማግኘቱ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ክልሉ በውስጡ ያለውን የህብረ ብሔሮች ብዝኃ ማንነት፣ የተፈጥሮ ሀብትና ቁሳዊ እሴቶች አጉልቶ ለማሳየት ትልቅ መድረክ ነው ብለዋል።