የከተማ ግብርና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰራተኞች ከመደጎም በተጨማሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የከተማ ግብርና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰራተኞች ከመደጎም በተጨማሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ እያስቻለ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት የተጀመረው የከተማ ግብርና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰራተኞች ከመደጎም በተጨማሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው የተቋሙ ሰራተኞች ገለፁ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት ባለፉት ሁለት አመታት እየተተገበረ ያለው የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር ተጨባጭ ለውጦችን እያስመዘገበ ይገኛል።
ተቋማትና ግለሰቦች ባላቸው ትርፍ ቦታ የእንስሳት እርባታና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትን በማካሄድ ምርታቸውን ከራሳቸው አልፈው ለገበያ ማቅረብ ችለዋል።
የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩትም መርኃ ግብሩን በመቀላቀል በተቋሙ ግቢ የጓሮ አትክልትና የዶሮ እርባታ እንዲሁም የንብ ማነብ ስራ እያከናወነ ይገኛል።
በኢንስቲትዩቱ የሆርቲካልቸር ዘርፍ አስተባባሪ ሰላማዊት አሰግድ ለኢዜአ እንዳሉት ባለፉት ሁለት አመታት በኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች እየተመረቱ ነው።
የኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች ከመደበኛ ስራቸው በተጓዳኝ አትክልቶችን በመንከባከብ ተጨማሪ ገቢ ከማግኘት ባለፈ በተመጣጣኝ ዋጋ በሚያገኟቸው ምርቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ብዝሃ ህይወት ምርምርና ጥበቃ ስራ ሂደት የለማዳ እንስሳት ቡድን አስተባባሪ አቶ አበበ ኃይሉ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በንብ ማነብና በዶሮ እርባታ ላይ መሰማራቱን ገልጸዋል።
ተግባሩ ለሰራተኛው ንፁህና ጥራቱን የጠበቀ ምርት ከማቅረብ ባለፈ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ሰራተኞች ለመደጎም ማስቻሉን ጠቁመዋል።
ኢንስቲትዩቱ በክረምቱ አንድ ሺህ ዶሮዎች በማስገባት ስራ መጀመሩንና አሁን ላይ 85 በመቶ ያህሉ እንቁላል መጣል መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ሁለት ወራት ለሰራተኞች በዝቅተኛ ዋጋ እንቁላል እየቀረበ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከእንቁላል ምርት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ የተጀመረውን ስራ ለማጠናከር እንደሚውልና ለዶሮ እርባታ ስራው አራት ሰራተኞች መቀጠራቸውንም ተናግረዋል።
ወይዘሮ ዘውድነሽ መኮንን በኢንስቲትዩቱ በፅዳት ስራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን በትርፍ ሰአታቸው በኢንስቲትዩቱ በተፈጠረላቸው የስራ እድል ኑሯቸውን እየደጎሙ ይገኛሉ።
ተቋሙ በጀመረው የከተማ ግብርና ስራ ላይ በመሰማራት ለተቋሙ ሰራተኞች ጥራታቸውን የጠበቁ የጓሮ አትክልቶች እያቀረቡ ለራሳቸውም እየተጠቀሙ መሆኑንም ገልጸዋል።
በኢንስቲትዩቱ በእፅዋት እንክብካቤ የሚሰሩት አቶ ተስፋዬ ይመር በበኩላቸው ላለፉት ሁለት አመታት ለተቋሙ ሰራተኞች ጥራቱን የጠበቀ ምርት እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች ስለአትክልት እንክብካቤ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ ችግኝ እያቀረቡ መሆኑንም ጠቁመዋል።