ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ወደ ኪንሻሳ አቀና 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታንዛንያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ለሚያደርጋቸው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ ኪንሻሳ ማምራቱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ጨዋታዎቹ ሕዳር 7 እና 10 ቀን 2017 ዓ.ም ይደረጋሉ።

የብሔራዊ ቡድኑ ጊዜያዊ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለማጣሪያ ጨዋታው ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ከጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል። 

ዋልያዎቹ በሞሮኮ በሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ አምስተኛ እና ስድስተኛ ጨዋታቸውን ለማድረግ ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ ወደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መዲና ኪንሻሳ ማቅናታቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምድብ 8 እስከ አሁን ባደረገቻቸው አራት ጨዋታዎች በሶስቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። ቡድኑ በጨዋታዎቹ እንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር ዘጠኝ ግቦችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በአንድ ነጥብ በምድቡ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃን ይዟል።

በዚሁ ምድብ የምትገኘው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያደረጋቻቸውን አራት ጨዋታዎች በማሸነፍ በ12 ነጥብ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፏን ማረጋገጧ የሚታወስ ነው።

ጊኒ በስድስት ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ታንዛንያ በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዋንጫው የማለፍ ተስፋዋን ለማለምለም የግድ ሁለቱን ጨዋታዎች ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

አልጄሪያ፣ ግብጽ፣ አንጎላ፣ ሴኔጋል፣ ቡርኪናፋሶ፣ ካሜሮን፣ ኮትዲቭዋር፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ እስከ አሁን በአፍሪካ ዋንጫው መሳተፋቸውን ያረጋገጡ ሀገራት ናቸው።

48 አገራት ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ በ12 ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።  

በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 24 አገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም