ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የገጠር ተቋማት ክላስተርን በማጠናከር ውጤታማ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ

ባህር ዳር፤ ህዳር 5/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የገጠር ተቋማት ክላስተር ዘርፍ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ውጤታማ የሚያደርጉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተገለጸ።

በዘርፉ የተደራጁ ተቋማት በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እያካሄዱ ነው።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በገጠር ክላስተር የተደራጁ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ትኩረት ተሰጥቷል።

ለዚህም በበጀት ዓመቱ የተያዙ እቅዶችን በጠንካራ ክትትልና ቅንጅት በመፈፀም ውጤት በሚያስመዘግብ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በመድረኩም እያንዳንዱ ተቋማት በሩብ በጀት ዓመቱ ያከናወኗቸውን አፈፃፀም ሪፖርቶች በማቅረብ ከመገምገም ባለፈ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡም አመልክተዋል።

እንዲሁም ተቋማቱ ለዘላቂ ሰላም መስፈን አወንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከት በሚችሉበት ጉዳይ ላይም ምክክር እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የቅንጅትና የጉድኝት አሰራሮች ያመጡትን ለውጥ በመገምገም በቀጣይ በተቋምና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ብቁ አመራርና ባለሙያ ለመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ላይ ውይይት ይደረጋል ብለዋል።

በመድረኩ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) እንዲሁም የክላስተር ተቋማት አመራር አባላትና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም