የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለያዩ አመላካቾች የላቀ ውጤት እየተመዘገበበት ነው - ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለያዩ አመላካቾች የላቀ ውጤት እየተመዘገበበት ነው - ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2017(ኢዜአ)፦ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለያዩ አመላካቾች የላቀና ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ የምጣኔ ሃብት እድገት እየተመዘገበበት መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ከምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን ኢኮኖሚ የገነባችው ኢትዮጵያ ከሰሐራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራትም የሦስተኛው ትልቁ የኢኮኖሚ ባለቤት ሆናለች።
ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ደግሞ የንግድና ኢንቨስትመንት መስኮችን ተወዳዳሪና ውጤታማ ለማድረግ፤ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ዐቅምን ማጠናከር፣ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብና አጠቃላይ የሀገርን የምጣኔ ሃብት እድገት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ነው።
በዚህም መሰረት የማሻሻያ ትግበራው በተለያዩ የኢኮኖሚ አመላካቾች አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገበበት መሆኑ ታውቋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፤ እንደ ሀገር የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉ ለኢኮኖሚ እድገት ማነቆ የነበሩ በርካታ ችግሮችን መፍታት አስችሏል ብለዋል።
በበጀት አመቱ ቀሪ ጊዜያት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተጀመሩ ስራዎች መሬት የሚይዙበት ወሳኝ ወቅቶች መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም መሰረት አሁን ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪና አጠቃላይ ገበያ እንዳይረጋጋ የሚያደርግ አንድም ምክንያት የለም ሲሉ አስረድተዋል።
በሩብ ዓመቱ በወጪ ንግድ፣ በገቢና በሐዋላ ፍሰት የታዩ ውጤቶች ጥሩ ማሳያ መሆናቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
ከወጪ ንግድ አኳያ በወርቅ የታየው አፈጻጸም ከፍተኛ መሆኑን አንስተው፥ በታንታለም የታየው ለውጥም የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ከግብ ለማድረስ አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑንም አክለዋል፡፡
በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በዲጂታል ዘርፎች የታዩ ውጤቶችም ለውጡ ፍሬ ማፍራት መጀመሩን ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
በግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ የምርት እድገት መኖሩ፣ በቱሪዝሙም በርካታ ዓለም አቀፋዊ ኮንፍረንሶችን ማስተናገድና በዲጅታል ዘርፍ የፈጠራ ስራዎች እየተስፋፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መንግስት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ጫና እንዳያሳድር የበጀት ድጎማ ሥርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ባለፉት ወራት የሸቀጦች የዋጋ ሁኔታ እየተረጋጋ መምጣቱንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል፡፡