ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሩብ ዓመቱ ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በስኬት አስተናግዳለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 5/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በአዲስ አበባ በስኬት ማስተናገዷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። 
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው፥ ሳምንታዊ ዐበይት የዲፕሎማሲ ክንውኖችንና ቀጣይ ተግባራትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል። 

በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ እንድትሆን ትልቅ ዕድል ፈጥሯል

"ከረሀብ ነጻ ዓለም" ዓለም አቀፍ ጉባዔ ረሀብን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ስኬታማ ውይይቶች የተደረጉበት ነው

በመግለጫቸውም፥ የኮንፈረንስ ዲፕሎማሲ፣ የሩሲያ አፍሪካ አጋርነት ፎረም የሚኒስትሮች ስብሰባ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እና የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ተግባራትን አብራርተዋል። 

በዚህም በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ኢትዮጵያ ከ30 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በአዲስ አበባ በስኬት ማስተናገድ ችላለች ብለዋል። 

ከርሃብ ነፃ ዓለም ጉባኤ፣ የካፍ ጉባኤ፣ ዓለም አቀፍ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ የአፍሪካ ንግድ ሚኒስትሮች ጉባኤና ሌሎች ኮንፈረንሶች ኢትዮጵያ በሩብ ዓመቱ ካስተናገደቻቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

ኮንፈረንሶቹ ኢትዮጵያ አቅሟን ያሳየችበትና የአዲስ አበባ ከተማም ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በማስተናገድ የዲፕሎማሲና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን ያስመሰከረችበት መሆኑን ተናግረዋል። 

በመድረኮቹም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገቢና ገጽታ ግንባታን ከማሳደግ ባሻገር ሁለንተናዊ የልማት ስኬቶቿን በልምድና ተሞክሮነት ማጋራቷን አብራርተዋል። 

በተለይም ከርሃብ ነፃ ዓለም ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የተሳተፉ የሀገራት መሪዎችና የተቋማት የስራ ኃላፊዎች የኢትዮጵያን ዘርፈ ብዙ የልማትና የለውጥ ውጤቶች መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በሩሲያ ሶቺ በተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ(ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል።

ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሴርጌ ላቭሮቭ እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጊዳዮች ላይ ስኬታማ ምክክር መደረጉን ተናግረዋል። 

በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ማብራሪያቸውም በቻይናዋ ጂያንሱ ግዛት ዋና አስተዳዳሪ ሹ ኩሊን የተመራ የግዛቷ ከፍተኛ  የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑክ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ መግባቱን አስታውቀዋል። 

ልዑካን ቡድኑ በአዲስ አበባ በሚኖረው ቆይታም የኢትዮ-ቻይናን በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በንግድና ኢንቨስትመንት ይበልጥ ለማጠናከር አይነተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ መንግስት ከሚያዚያ 14/2016 እስከ ጥቅምት 2017 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 94 ሺህ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለሱን አስታውቀዋል። 

በሊባኖስና ማይናማር በአስቸጋሪ ሁኔታ የነበሩ ዜጎችን የመመለስ ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል። 

ኢትዮጵያውያን በህገወጥ ደላሎች ከመታለልና የስራ ስምሪት ስምምነት ሳይደረግ ከሚደረግ ጉዞ መቆጠብ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም