የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትን ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው - ኢንጂነር ጌታቸው አረጋ - ኢዜአ አማርኛ
የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትን ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው - ኢንጂነር ጌታቸው አረጋ
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 4/2017(ኢዜአ)፦የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትን ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ጌታቸው አረጋ ገለጹ።
በጎንደር ከተማ ህዝብ ለረጅም ጊዜ ቅሬታ ሲያነሳባቸው የቆዩት የጎንደር አዘዞ መንገድ፣ የመገጭ ግድብ እንዲሁም የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስት ዕድሳት እና የመስቀል አደባባይ-ጃንተከል ዋርካ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጭነት በመፋጠን ላይ ይገኛሉ።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፤ በከተማዋ ሌት ተቀን እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች አዲስ የስራ ባህልን እየፈጠሩ ናቸው ብለዋል።
በፕሮጀክቶቹ በርካታ ዜጎች እየተሳተፉ ሲሆን በስራ ዕድል፣ በገቢና በእውቀት ሽግግር ተጠቃሚ መሆናቸውንም ነው ያነሱት።
በክትመት ልምምድ የኢትዮጵያ አብነት የሆነችው የጎንደር ከተማ የመሰረተ ልማት ስራዎች የዜጎችን የዘመናት ጥያቄ የሚመልሱ፤ በፌደራልና በክልል መንግስት ልዩ ድጋፍ የሚደርግባቸው ናቸው ብለዋል።
በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጎንደር ከተማን ውብ ገፅታ ለማላበስ አይተኬ ሚና ላላቸው የመሰረተ ልማት ስራዎች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አንስተዋል።
ከከተማ ውስጥ የኮሪደርና ሌሎች መሰረተ ልማት ሥራዎች ባሻገር ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት እየተገነባ የሚገኘው የመገጭ ግድብም በመፋጠን ላይ ይገኛል።
በመገጭ ግድብ ግንባታ የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ተወካይ ታመነ ዳኘው፤ ፕሮጀክቱ ለ15 ዓመታት ያህል እዚህ ግባ በማይባል የግንባታ ሂደት ችግር ውስጥ ወድቆ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከሐምሌ 01/2016 ዓ.ም ጀምሮ ቢአኤካ ለተሰኘ አዲስ የግንባታ ተቋራጭ በመስጠት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ የሚያስችል ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ለጎንደር ከተማ 34 ሚሊዮን ሜትር ኩዩቢክ የንጹህ መጠጥ ውሃ የማቅረብ እና 17 ሺህ ሄክታር መሬትን በመስኖ የማልማት አቅም ይኖረዋል ብለዋል።
ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ተቋራጭም ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የመገጭ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ጌታቸው አረጋ፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ለጎንደር ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ለመስኖ ልማትና ለዓሳ እርባታ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ለዚህም ፕሮጀክቱን ከነበረበት ውስብስብ ችግር በማላቀቅ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ለማጠናቀቅ ቀን ከሌሊት ያለምንም እረፍት የግድቡ ግንባታ እየተፋጠነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በቢአኤካ ጠቅላላ ንግድ ስራ ድርጅት በጎንደር ከተማ የሚያስገነባቸው ሶስት ፕሮጀክቶች አስተባባሪ ላቃቸው እንየው፤ የመገጭ ግድብ ፕሮጀክትን ማሳለጥ የሚያስችል ማሽን በመትከል በተደራጀ የሰው ኃይል እየተሰራ ነው ብለዋል።
የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክትም ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፈጠሩንም ተናግረዋል።
ግድቡ ሲጠናቀቅ የጎንደር ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማሻሻል የደንቢያና ማክሰኝት ወረዳ አርሶ አደሮችን በመስኖ ልማት ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸውም ነው ያነሱት።
በመገጭ ግድብ ግንባታ የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል አቶ አነጋግረኝ አለሙ፤ የግድቡ ግንባታ መጓተት እንደ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሮብን ቆይቷል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓትም በተለያየ የሙያ መስክ በተፈጠረላቸው የስራ ዕድል የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ በታላቅ ተነሳሽነትና በባለቤትነት ስሜት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ሌላኛው የመገጭ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የስራ ዕድል ተጠቃሚ መልካሙ አሰፋ፤ ፕሮጀክቱ መልሶ ስራው በተጀመረ በቅርብ ወራት ውስጥ ከፍተኛ የግንባታ ለውጥ ላይ እንደሚገኝ አውስቷል።
በአሁኑ ሰዓት ከፈጠረላቸው ጊዜያዊና ቋሚ የስራ ዕድል ባሻገርም ግድቡ ሲጠናቀቅ በመስኖ ልማት፣ በዓሳ እርባታና በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተስፋቸውን ተናግሯል።