ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት ያላት ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው- ታሪዬ ባድጌሲን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት ያላት ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው- ታሪዬ ባድጌሲን
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2017(ኢዜአ):-ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት ያላት ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ሲሉ የ“ክላይሜት ኢንቨስትመንት ፈንድ' ዋና ስራ አስፈጻሚ ታሪዬ ባድጌሲን ተናገሩ።
29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) በአዘርባጃን ባኩ መካሄድ ከጀመረ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴን (ዶ/ር) ጨምሮ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በጉባዔው ላይ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።
ፕሬዝዳንት ታዬ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና በአካባቢ ጥበቃ እየሰራች ያለችውን ስራ የሚያሳይ መካነ ርዕይ (ፓቪሊየን) መርቀው መክፈታቸው ይታወቃል።
የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔው ተሳታፊዎች መካነ ርዕዩን በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ።
በ “ክላይሜት ኢንቨስትመንት ፈንድ” (Climate Investment Fund) ዋና ስራ አስፈጻሚ ታሪዬ ባድጌሲን የተመራ ልዑካን ቡድንም በመካነ ርዕዩ ጉብኝት አድርጓል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከዋና ስራ አስፈጻሚዋ ጋር በደን ልማት ላይ ያተኮረ የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
ባድጌሲን ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም ለመገንባት ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ፥ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ እና ልዑካቸው መካነ ርዕዩን በመጎብኘታቸውና ውይይት በማድረጋቸው ምስጋና ማቅረባቸውን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።