#ኮፕ-29 እና ምላሽ የሚሹ ድምጾች - ኢዜአ አማርኛ
#ኮፕ-29 እና ምላሽ የሚሹ ድምጾች
በአየለ ያረጋል
ስለአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ መባባስ ማውሳት ለቀባሪው ማርዳት ይመስላል። በሰው ሰራሽ ተጽዕኖ ሳቢያ ተፈጥሮ ይዘቷ መዛባቱ ዕሙን ነው። የምድራችን ጤነኛ መልክ ወይቧል። ብዝሐ ሕይወቷ ተመናምኗል። ለጉዳዩ አስቀድሞ ትኩረት ባለመሰጠቱ ተጽዕኖው የዛሬውን ትውልድ እየቀጣ ለመጪው ትውልድ ደግሞ የተጎሳቆለች ዓለምን እና ዕዳን እያስተላለፈ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበትን ቀጣና ጨምሮ በዓለም ላይ በየዕለቱ ተፈጥሯዊ አደጋና ሰቆቃ መስማት የተለመደ ጉዳይ ሆኗል። የረጋው መሬት ይክዳል። ዝናብ ወቅቱን ማዛነፍ ከጀመረ ሰነባብቷል። ወጀቡም፣ ሰደዱም አይሏል። ሙቀቱ፣ በርሃማነቱ፣ ድርቅና ርሃቡ ከምንግዜውም በበለጠ ተባብሷል።
በዚህ መሀል ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሰባሰበው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (በእንግሊዝኛው Conference of Parties-CoP) ለ29ኛ ጊዜ እየተካሄደ ነው። ከትናንት በስቲያ በአዘርባጃኗ ባኩ ከተማ በይፋ የተከፈተው ኮፕ-29 ውለው ያደሩ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎችን አዝሏል። አዳዲስ መፍትሔ-ጠሪ ድምጾች ይንጸባረቁበታል።
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጉባዔው መክፈቻ ላይ “ዘንድሮ ክብረ ወሰን የሰበረ የምንጊዜም ሞቃታማው ዕለት፣ ወርኅና ዓመት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። የዘንድሮ ዓመት ‘ምንጊዜም ሞቃቱ’ ከተባለ ደግሞ ከርሞ እና ቀጥሎ ባሉት ዓመታት ይበልጥ ይባባሳል እንጂ አይቀዘቅዝም። ጉተሬዝ የጉዳዩን እጅግ አስፈሪነት እና አሳሳቢነት በማውሳትም “ለችግሩ መፍትሄ ላይ የምንደርስበት ጊዜው አሁን ነው” ሲሉ ጉባዔተኞችን ተማፅነዋል።
ኮፕ ለሦስት አስርት ዓመታት በየዓመቱ ቢካሄድም በተጨባጭ የመፍትሔ ማዕከልነቱ ግን ብዙሃኑን አላረካም። የነገረ-አየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ የገደዳቸው ተሟጋቾች እና በተለይም የችግሩ ዐቢይ ሰለባ የሆኑት ታዳጊ ሀገራት ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም። የዓለም የተፈጥሮ ሚዛንን በሚያስጠብቁ ነባር ማህበረሰቦች ጥያቄው ሲበረታ እና ለምድርና ከባቢ አየር ብክለት ከፍተኛ ሚና ያላቸው የዓለማችን አድራጊ ፈጣሪዎች ደግሞ በጉዳዩ ቸልተኛ መሆናቸው ችግሩን አወሳስቦታል። መልከ-ብዙ ዝርዝር ይዘቶችን ያቀፈው የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ጉዳይ የዘንድሮው ጉባዔ(ኮፕ-29) ቁልፍና አንገብጋቢ አጀንዳ ነው።
አቶ ዳሞ በለጠ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጉራጌ ዞን ነዋሪ ሲሆኑ በሰላም፣ በፍትሕ፣ በዳኝነት፣ በአካባቢ ጥበቃና በሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰራው የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ(የጆካ ቂጫ) ጸሐፊም ናቸው።
በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ የጆካ እና ለአካባቢ ጥበቃ ሁነኛ ተምሳሌት የሆነው ጀፎረ(የጉራጌ ባህላዊ ጎዳና) መካከል ነባርና ታሪካዊ ትስስር እንዳለ ያነሳሉ። የአየር ንብረት ለውጥ ከሰፈር እስከ ጠፈር እንዴት መልክዓ-ዓለምን እየተፈታተነ እና በሰዎች ሕልውና ላይ አደጋ እንደደቀነ አቶ ዳሞ ተረድተዋል።
እርሳቸው ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ማህበረሰብም ሆነ ሸንጎው የተፈጥሮ ሀብትና የአካባቢ ጥበቃ የኑባሬያቸው አካል ቢደረግም ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ግን እንዳላመለጡ ይገልጻሉ። የገጠሩ ማህበረሰብ ተፈጥሮን የሚጎዳበት ዕድል እምብዛም ቢሆንም የገፈቱ ግንባር ቀደም ተጠቂ ሆኗል ባይ ናቸው።
“በጉራጌ ባሕል ዛፍ መትከል የተለመደ ነው። አካባቢ መጠበቅ ባህል ነው። በጀፎረ የምታያቸው ዝግባ፣ ጽድ፣ ወይራና መሰል ዛፎች(በጣታቸው በመጠቆም) ለዚህ ምስክር ናቸው። ዛፍ ሲቆረጥ እንኳን ሌላ ተተክቶ ነው። ንጹህ አየርና ጤናማ ኑሮ የሚያመጡ ዛፎች መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብ ባህል ነው። ገጠሩ ማህበረሰብ አካባቢን አይጎዳም። ሌላውን ዓለም ግን ተመልክተው አየር እየበከለ ነው። ‘አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ’ ነው የሆነብን። ያደጉ ሀገራት በሚያደርሱት ጫና የጉዳቱ ሰለባ እኛ ነን። እኛ ጥሩ አረንጓዴ አካባቢ ብንፈጥርም በሌሎች ምክንያት እየተጎዳን ነው። ለዚህ ካሳ እንፈለጋለን። እኛ ለአካባቢ ጥበቃ የምናወጣው ወጪ፣ ጊዜ፣ ጉልበት ከምስጋና ጋር የጉዳት ካሳ መከፈል አለበት። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየጊዜው በሚደረጉ ስብሰባዎች ይህ ጉዳይ ይነሳል። መክፈል የሚገባቸው ወገኖች ይህን ለማድረግ ምን ያዳዳቸዋል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
የአቶ ዳሞ ጥያቄ በእርሳቸውና አካባቢያቸው ብቻ የተወሰነ አይደለም። ይልቁኑም የሁሉም ነባር ማህበረሰብ ክፍሎች መሻት፣ አፍሪካን መሰል ታዳጊ ክፍላተ ዓለማት ጩኸት ብሎም የመጻዒው ዓለም እና ትውልድ ዕጣ ፈንታ የሚገዳቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድምጽ ነው።
የሁሉም ማህበረሰብ ክፍል ተወካዮች በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ተሰባስበው ምላሽ ያላገኘ ድምጻቸውን የሚያሰሙትም ለዚህ ነው። ምክንያቱም የኮፕ መድረክ ዓለምን ክፉኛ እየፈተነ በሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ መፍትሄ ለማበጀት የሀገራት መሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት፣ የሚደራደሩበትና የጋራ ውሳኔ የሚተላለፍበት መድረክ ነውና።
በኮፕ-29 ከመድረኩ በተጓዳኝ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሀገራት የየራሳቸው መካነ ርዕይ ይዘው ይሳተፋሉ። በዚህም የድርድር አጀንዳቸውን የሚሸጡበት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ግንባታን ተሞክሯቸውን የሚያጋሩበት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዘላቂ አጋርነት የሚመሰርቱበትም ነው። የአካባቢና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን የሚያሳዩበትና የተጽዕኖ መቋቋም ጥረታቸውን የሚያስቃኙበት አጋጣሚም ነው።
አቶ እንዳሻው ሞገሴ በሥነ ሕዝብ፣ ጤና እና አካባቢ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ 99 ሲቪል ማህበራትን ያቀፈው ፒ.ኤች.ኢ.ኢ.ሲ የተሰኘው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ዋና ዳይሬክተር ናቸው። ጥምረቱ ከተመሰረተ ጀምሮ ላለፉት ዓመታት ከኮፕ-15 ጀምሮ በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች ተሳትፎ ላይ የካበተ ልምድ እንዳለው ይናገራሉ። ዘንድሮው በአዘርባጃን ባኩ እየተካሄደ ባለው የኮፕ መድረክም ተሳታፊ ናቸው።
አቶ እንዳሻው ካላቸው ልምድና ትዝብት በመነሳት “ኮፕ መካሄድ ከጀመረ 30 ዓመታት ቢያስቆጥርም የተላለፉ ውሳኔዎች ተፈጻሚነት አናሳ ነው፤ ሀገራት የሚጠበቀውን ያህል ሲተገብሩና ሲያሳኩ አይታይም” ይላሉ።
በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የሚፈጠሩ ችግሮች በየጊዜው እየተባባሱና የሚነኳቸው ዘርፎችም እየሰፉ መጥተዋል። ለአብነትም በጤና ነክ ጉዳዮች የወጣቶች፣ ህጻናትና ሴቶች ተጎጂነት ጨምሯል። በአቶ እንዳሻው እምነት ይህ ሊሆን የቻለው በኮፕ መድረኮች ውሳኔዎችን የሚፈራረሙ ሀገራት የገቡትን ግዴታ ባለመፈማቸው እንደሆነ የፓሪሱን ስምምነት ለአብነት ያነሳሉ።
“በፓሪስ ስምምነት ያደጉ ሀገራት በየዓመቱ 100 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቢስማሙም ስምምነቱ በልኩ አልተፈጸመም። ይህ ደግሞ ኮፕ መፍትሄ አለማምጣቱን ማሳያ ነው።” ይላሉ።
የዘንድሮው ኮፕ-29 በአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ(Climate Finance) ላይ እንደሚያጠነጥን በመጥቀስ፣ የእስከዛሬ የኮፕ መድረኮች ተጨባጭ ለውጥ ባያመጡም መሳተፉ፣ ድጋፍ ለማጠናከርና አጋርነት ለማደርጀት ይበጃል የሚል እምነት አላቸው።
በሌላ በኩል በኮፕ መድረኮች የተንጠለጠሉ ወይም ያልተቋጩ አያሌ ጉዳዮች፣ እልባት ያላገኙ ረቂቅ ሰነዶችና ስምምነቶች እንዳሉ በመጥቀስ፣ በዘንድሮው ጉባዔ እልባት ያገኛሉ የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።
ለአብነትም የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ አካል የሆነው የታዳጊ ሀገራት ጉዳት ካሳ(Loss and Damage) ጉዳይ ላይ አንድ ውሳኔ እንደሚተላለፍ ይጠብቃሉ።
“የቦረና ድርቅ ምን ያህል ከብቶችን እንዳሳጣ ማንሳት እንችላለን። ሌሎች ሀገራት ባደረሱት የብክለት አበርክቶ የቦረና አርብቶ አደሮችን ዋጋ እያስከፈለ ነው። ይህ ድርቅ የጉዳት ካሳ ይፈልጋል። ስለዚህ ይህ ወደ ትግበራ እንዲገባ በዘንድሮው ኮፕ እጠብቃለሁ። ከስርዓተ ጾታ ጋር የተያያዙ አካታች የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች እና ረቂቅ የስምምነት ማዕቀፎች አሉ። ይህ ጉዳይም ከስምምነት ይደረሳል የሚል ተስፋ አለኝ” ብለዋል።
በኮፕ መድረክ ተደራዳሪዎቹ መንግስታት ስለሆኑ የሲቪል ማህበራት ሚና የሚመለከታቸውን አካላት ማነጋገር፣ ሃሳባቸውን መሸጥና የድርድር አካል እንዲሆኑ ማስገንዘብ ብቻ ነው። በዘንድሮው ኮፕ መድረክ ሲቪል ማህበራቱ ከኢትዮጵያ ልዑክ ጋር በመሆን በተጓዳኝ ሁነቶች በንቃት የመሳተፍ፣ ከአቻ ሲቪል ማህበራት ጋር የመነጋገርና ተሞክሮ የመጋራት ብሎም ሃሳቦች የስምምነት አካል እንዲሆኑ ተጽዕኖ ለማሳደር ተዘጋጅተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ መባባስ የመንግስታትን ዕቅዶችና የሀገራትን ዘላቂ ልማትን እያጓተተ መሆኑን አቶ እንዳሻው ይገልጻሉ። በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የሚደርሱ አደጋዎች የልማት በጀቶችን እየተሻሙ ነው ብለው ያምናሉ። ለአብነትም ለጤና መሰረተ ልማት የሚሆኑ በጀቶች ለድርቅ፣ ለጎርፍና ለሌሎች ቀውሶች አስቸኳይ ርዳታ እየዋሉ በመሆኑ የጤና ተቋማትን ከማጠናከር ይገድባል። ልማትና ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ በተለይም በታዳጊ ሀገራት የከፋ ተጽዕኖ ያደርሳል። በአቶ እንዳሻው ዕይታ ጉዳዩ የተቀናጀ ስራና መፍትሄ ይሻል።
ለምሳሌ ድርጅታቸው የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይን ከጤናና ስነ ተዋልዶ ጋር አዛምዶ እንደሚሰራ ያነሳሉ።
ወጣት እስከዳር አውግቸው ደግሞ የሥርዓት ምህዳር ፍትህ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል ሲቪል ማህበረብ ድርጅት መስራችና ዋና ዳይሬክተር ነው። ድርጅቱ የአየር ንብረት ለውጥ ፍትሕ ያስፈልጋል በሚል የተቋቋመ ነው።
“ባደጉ ሀገራት በሚመነጭ የሙቀት አማቂ ጋዞች ችግር ተፅዕኖ የመቋቋም አቅም በሌላቸው ሀገራት ላይ ያርፋል። ለዚህ ኢትዮጵያ ማሳያ ናት። ከመጠን በላይ ዝናብና ድርቅ እየፈተነን ነው። ይህን መሰል ጉዳት ለመቋቋም ሃላፊነት የታከለበት ካሳ በተመጣጣነ ሁኔታ ይኑር ነው ጥያቄው” ይላል። ድርጅታቸው በተመድ ዕውቅና የተሰጠው መሆኑን በመጥቀስም፤ በሌላው የዓለም ክፍል ካሉ አቻ ማህበራት በመቀናጀት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጿል።
የዘንድሮውን ኮፕ በተመለከተም “ከኮፕ 29 እስካሁን የተደረጉ ድርድሮች ወደ እርምጃ እንዲገቡ እንጠብቃለን” ይላል። መድረኩ ወጣቶችን ያሳተፈ እና ዓለምን የሚረከበውን ወጣት ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ስምምነቶች እንደሚወጡበትም ተስፋ ሰንቋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ሶስት ወሳኝ ቃላት እንዳሉ እስከዳር ያነሳል። ይሄውም ቅድመ መከላከል( ሚቲጌሽን)፣ ተጽዕኖ መቋቋም (አዳፕቴሽን) እንዲሁም የጉዳት ካሳ(ሎስ ዳሜጅ) የሚሉ ናቸው። ዳሩ የእርምጃዎች ገቢራዊነት መዘግየት ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለ እንደሆነ ያብራራል። ለምሳሌ የአየር ንብረት ለውጥ እንዳይመጣ መከላከል( ሚቲጌሽን) የሚለው ግብ ዛሬ ላይ ጊዜው አልፏል። ዓለም ክፉኛ እየተጎዳች ነውና። ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መቋቋም ፍትህ ይጠይቃሉ፤ የጉዳት ካሳም እንዲሁ።
በጥቅሉ የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠረው ምድራዊ ምስቅልቅልና የደቀነውን የባሰ ስጋት ለመግታት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለመፍትሄዎቹ ጊዜ መስጠት እንደሌለበት ግልጽ ነው።
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጎቴሬዝ ባኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ችሮታ ሳይሆን ኢንቨስትመንት ነው። የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ ስምምነቶች ትግበራም አማራጭ ሳይሆን አስገዳጅ ነው።
ዋና ፀሐፊው ሞቃታማና የውድመት ዓመት ባሉት የፈረንጆቹ 2024 አውሎ ነፋስ የበርካቶቹን ነፍስ መንጠቁን፣ የብዝሐ ሕይወት መመናመነን፣ ከልክ ያለፈ ሙቀት የበርካታ ሠዎችን ህይወት መቅጠፉን፣ ደራሽ ጎርፍ ብዙ የማህበረሰብ ክፍልን ለመከራ መዳረጉን፣ በሰብል አውዳሚ ድርቅ ልጆች ያለዕድሜያቸው በረሀብና ቸነፈር አለንጋ መገረፋቸውን… ዘርዝረዋል። በየትኛውም ክፍላተ ዓለም ኑሮ መወደዱን፣ ዋጋ መናሩን፣ መጠለያዎች መውደማቸውንም እንዲሁ። ከዚህ ሁሉ ቀውስ የተረፈ ሀገር የለም ብለዋል።
“ያም ሆኖ አሁንም ተስፋ አለው” ሲሉ ቃል የተገቡ ስምምነቶች ገቢራዊ እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል። በተለይም መንግስታት ኢኮኖሚያቸውን ከነዳጅ ይልቅ በታዳሽ ኃይል ላይ እንዲመሰረቱ፣ የዓለም ሙቀት መጠንን ከአንድ ነጥብ አምስት ዲግሪ ሴልሼስ መገደብን ጨምሮ የአየር ንብረት ግቦችን በየሀገራቸው የዕቅድ አካል አድርገው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
የዘንድሮው ጉባዔ (ኮፕ-29) የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ላይ መክሮ እልባት እንዲሰጥም ጠይቀዋል። ለዚህ ስኬት ደግሞ ትኩረት ይሻሉ ያሏቸውን ነጥቦች ዘርዝረዋል።
ይኸውም ለዘላቂ ልማት የሚውል ከለጋሾች የሚሰበሰብ ገንዘብን የማሳደግ አስፈላጊነት፣ የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደቱን ለታዳጊ ሀገራት ፍላጎት በሚሸፍን መልኩ በግልጽ የማመላከት፣ የአየር በካዮች በተለይም የመርከብ፣ የአየርና የነዳጅ አውጭዎች ገንዘብ የሚከፍሉበትን አዳዲስ ዘዴ መቀየስ፣ የገንዘብ ድጋፉ ተደራሽነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው አግባብ የሚተገበርበትን ማዕቀፍ ማውጣት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን የልማት ባንኮች የማበደር አቅማቸውን የሚያጎለብቱበትን ሁኔታ ማመቻቸት የሚሉ ሃሳቦችን አንስተዋል።
ይቆየን!