ኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ ግብርና በብሔራዊ የአየር ንብረት ፖሊሲዋ ውስጥ በማቀናጀት የምግብ ዋስትናን እና የአካባቢ ጥበቃን ለማሳደግ እየሰራች ነው -ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ ግብርና በብሔራዊ የአየር ንብረት ፖሊሲዋ ውስጥ በማቀናጀት የምግብ ዋስትናን እና የአካባቢ ጥበቃን ለማሳደግ እየሰራች ነው -ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ ግብርና በብሔራዊ የአየር ንብረት ፖሊሲዋ ውስጥ በማቀናጀት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የአካባቢ ጥበቃን ለማሳደግ እየሰራች እንደምትገኝ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በአዘርባጃን እየተካሄደ በሚገኘው 29ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ 29) የዓለም መሪዎች የተገኙበት የከፍተኛ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ እና የምግብ ስርዓት እና የተፈጥሮ ማገገም ላይ ያተኮረ ስብሰባ አድርጋለች።
በስብስባው ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የአየር ንብረት ለውጥ እና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር አምና ቢንት አብዱላህ አል ዳሃክ አል ሻምሲ (ዶ/ር) ፣ የኮፕ 29 ፕሬዝዳንት እና የአዘርባጃን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሚኒስትር ሙክታር ባባዬቭ እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።
ስብሰባው የዓለምን የሙቀት መጠን ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ እንዳያልፍ የተያዘውን የአየር ንብረት ግብ ማሳካት እንዲሁም የምግብ ስርአቶችንና የመሬት አጠቃቀምን ማሻሻል ያለው አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ነው።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ኢትዮጵያ ዘላቂ የሆነ ግብርና በብሔራዊ የአየር ንብረት ፖሊሲዋ ውስጥ በማቀናጀት የምግብ ዋስትናን እና የአካባቢ ጥበቃን ለማሳደግ ቁርጠኛ ናት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ትልቅ የአየር ንብረት እርምጃ ከአርሶ አደሮች ኢኮኖሚያዊ ዕድሎች ጋር የተጣመረ መሆኑ የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚያስችል አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ትርጉም ያላቸው መፍትሔዎችን ለማራመድ እና ዓለም አቀፍ አቀፍ አጋርነቶችን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗ ተገልጿል።
በስብሰባው የካርበን ልቀትን መቀነስ፣ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ ማቋቋም እና ዘላቂ ግብርናን ማስፋት አስፈላጊ እንደሆነ መነሳቱን ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።