ቀጥታ፡

የበደሉትን ህዝብ ለመካስ ቁርጠኛ ሆነው ከጥፋት አካሄድ መመለሳቸውን እጃቸውን የሰጡ ታጣቂዎች ገለጹ

መተማ፤ ህዳር 4/2017(ኢዜአ)፡- በፈጸሙት ጥፋት በመፀፀት የበደሉትን ህዝብ ለመካስ ቁርጠኛ ሆነው ከጥፋት አካሄድ መመለሳቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን ለመንግሥት እጃቸውን የሰጡ ታጣቂዎች ገለጹ።

እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ስራ ውጤት እየተገኘ ከመሆኑ ባሻገር በርካቶች ከነትጥቃቸው እጃቸውን ለመንግሥት እየሰጡ ይገኛሉ።


 

እጃቸውን ከሰጡት መካከል ተመስገን አበበ በሰጠው አስተያየት፤ በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ህዝብን ሲበድሉና ሲያሰቃዩ መቆየታቸውን አስታውሷል።

ለወንጀለኛ ግለሰቦች መጠቀሚያ ሆነን ቆይተናል ያለው ተመስገን፤ የንብረት መዝረፍ፣ ማውደምና የሰው ህይወት መቅጠፍ የፅንፈኛ ኃይሉ ዋነኛ ተግባር መሆኑን ተናግሯል።

የአማራን ብሎም የኢትዮጵያን ህዝብ አንገት ያስደፋ አስነዋሪ ተግባር ውስጥ የቆዩ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ በቀጣይ የበደለውን ህዝብ ለመካስ መዘጋጀቱን አስታውቋል።


 

ሌላው እጁን የሰጠው ፋሲል ሸጋው በበኩሉ፤ የአማራ ህዝብን በማይመጥን ተግባር በመሳተፍ ከፍተኛ በደልና ኪሳራ ሲያደርስ እንደነበር ተናግሯል።

ያሳደገንን ማህበረሰብ ገለናል፤ ሀብት ንብረቱን ዘርፈናል፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ ያለው ፋሲል፤ በቀጣይ ህዝብን የሚክስ ስራ ለመስራት ቁርጠኛ ሆኖ መመለሱን ገልጿል።

የፅንፈኛ አመራሮች እጃችሁን ለመንግሥት ከሰጣችሁ ትረሸናላችሁ በሚል የውሸት ፕሮፖጋንዳ አጉል መስዋዕትነት አስከፍለውናል ያለው ደግሞ ታደሰ ደማስ ነው።

እጃቸውን ከሰጡ በኋላ ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ በእንክብካቤ መያዛቸውን አመልክቶ፤ ሌሎች ታጣቂዎችም በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን በመስጠት ህዝብን ከመበደል እንዲቆጠቡም መልዕክት አስተላልፏል።


 

በሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ504ኛ ኮር ምክትል አዛዥና ለውጊያ አገልግሎት ድጋፍ ኃላፊ ኮሎኔል ቾምቤ ወርቁ እንደገለጹት፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከጥምር የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን እየወሰደ ባለው የህግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ በርካታ ድሎችን እያስመዘገበ ነው።

መከላከያው ከሰላም ወዳዱ ህዝብ ጋር በመሆን የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅና ከፅንፈኛው የፀዳ ለማድረግ በትጋት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተከናወነው የተጠናከረ ስራም የፅንፈኛ ቡድኑን አጥፊነትና አውዳሚነት በመገንዘብ እስከነ ትጥቃቸው እጃቸውን እየሰጡ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የተጀመሩ ተግባራትም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በህግ በማስከበር ስራው በርካታ ቀበሌዎችን ከፅንፈኛው ማፅዳት ተችሏል ያሉት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አንዳርጌ ጌጡ ናቸው።

ፅንፈኛ ቡድኑ አሁን ላይ በጥምር ኃይሉ በደረሰበት ምት መፈረካከስ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ፅንፈኛውን ለማፅዳት ከውስጥ የማጥራት ስራ መጀመሩን አመልክተው፤ በከተማ ሆነው መረጃ የሚያቀብሉ 200 የሚደርሱ የፅንፈኛ ሴሎችን በህግ ጥላ ስራ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

መንግስት ለሰላም በሰጠው ቅድሚያ 152 ታጣቂዎች እጃቸውን መስጠታቸውን ገልጸው፤ 83 የሚሆኑት ከነሙሉ ትጥቃቸው መግባታቸውን አስታውቀዋል።

የሰላምን አመራጭ ለተከተሉ ሁሉ ተገቢውን ተሀድሶ በመስጠት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም