ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ዘርፍ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ፤ህዳር 4/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥናትና ምርምር ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) ፈርመዋል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ጉባኤው በሀገሪቱ ለሁለንተናዊ ሰላም ግንባታ በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እየተወጣ ነው።


 

ጉባኤው ስራዎቹን በጥናትና ምርምርም ለመደገፍ ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ጋር የትብብር ስምምነት መፈራረሙን ነው የገለጹት።

ዩኒቨርሲቲው በአገሪቱ አንጋፋ በመሆኑ ያለውን ሰፊ ልምድ በመጠቀም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ምርምሮችን የሚያደርግ በመሆኑም ጉባኤው በጋራ ለመስራት መፈለጉን ነው የጠቀሱት።

የአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ተማሪዎች በስነ-ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር በርካታ ልምዶችን ሲያካብት መቆየቱን ነው የገለጹት።

ይሕንኑ ልምድ በመጠቀም ጉባኤው በሀገሪቱ በዘላቂ ሰላምና በትውልድ ግንባታ ላይ የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍም በስምምነቱ መሰረት ጥናትና ምርምሮችን እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም