ቀጥታ፡

የብራዚል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማምረቻ እና የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ዘርፎች እንዲሠማሩ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2017(ኢዜአ)፦ የብራዚል ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በማምረቻ እና የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ዘርፎች እንዲሠማሩ በብራዚል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ጥሪ አቅርበዋል።

አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ከብራዚል የንግድ እና የቢዝነስ ምክር ቤቶች ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አልፍሬዶ ኮንቴ ኔቶ ጋር የኢትዮጵያ እና የብራዚልን የኢኮኖሚ ትብብር ዘርፎች ማጠናከር የሚያስችል ውይይት አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፣ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች እና ለኢንቨስትመንት ምቹ የመሰረተ-ልማት፣ የሰው ሃይል እና የሥራ ከባቢ፣ የግሉ ዘርፍ ለልማት እንዲሳተፍ የተመቸ ሀገራዊ አመራርና ቁርጠኝነት መኖሩን ለኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቱ ገልጸውላቸዋል።


 

በኢትዮጵያ የውጭ ባለሃብቶች በማምረቻው እና የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ዘርፎች መሰማራት የሚያስችሉ በርካታ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸውንና የነጻ ንግድ ቀጣና ዞኖች መዘጋጀታቸውን ማሳወቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ብራዚል እና አካባቢው የሚያደርገውን የየዕለት የመንገደኞች እና የካርጎ በረራ ለአልሚዎች ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም አምባሳደር ልዑልሰገድ ጨምረው አብራርተዋል።

የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አልፍሬዶ ኮንቴ ኔቶ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ያላት መሆኑን መገንዘባቸውንና ይህንን ወደ ተጨባጭ የኢትዮ-ብራዚል የንግድ ግንኙነት ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ኮንፌዴሬሽኑ ከኤምባሲው ጋር በመተባበርና በቅርበት እንደሚሰራ መግለጻቸው በመረጃው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም