ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ጉብኝት እየተከናወነ ነው 

ባህር ዳር  ፤ ህዳር 3/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ከተሞች የተጀመሩ የኮሪደር ልማቶች በምሽት ጭምር እየተሰሩ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ ገለፁ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ ሌሎች አመራር አባላት በባህር ዳር ከተማ እየተሰራ የሚገኘውን የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እንቅስቃሴ ዛሬ ምሽት እየጎበኙ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አረጋ  በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት፤ በክልሉ ባህር ዳርን ጨምሮ በስምንት ዋና ዋና ከተሞች የኮሪደር ልማት እየተከናወነ ይገኛል።

የኮሪደር ልማት ስራ የከተሞችን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለበርካታ ወገኖች የስራ እድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በየደረጃው ያለው አመራር አባል በችግር ውስጥም ሆኖ የኮሪደር ልማትና ሌሎች የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ተግባራት በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል። 

የኮሪደር ልማት ተግባራት የስራ ባህልን በመቀየር በምሽት መስራት እየተለመደ መምጣቱን ያብራሩት አቶ አረጋ፤ ይህም የአመራር አባላቱና የሰራተኛው ቁርጠኝነት የታየበት እንደሆነም ገልጸዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የከተማና መሰረት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አህመዲን መሃመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ 47 ኪሎ ሜትር በላይ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ለማልማት ታቅዶ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የኮሪደር ልማት ሰው ተኮርና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህ ልማትም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

በምሽት በተካሄደው የኮሪደር ልማት ጉብኝት የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላት እየተሳታፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም