ተማሪዎች ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያፈልቁ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ተማሪዎች ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያፈልቁ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2017(ኢዜአ)፦ ተማሪዎች ለሀገር እድገት ከፍ ያለ ሚና ያላቸውና ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያፈልቁ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑ ተገለጸ።
የትምህርት ሚኒስቴር፣ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፣ከስቴም ፓወር ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅትና እና ሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 9ኛው አገር አቀፍ የሳይንስና ኢንጂነሪንግ የፈጠራ ሥራዎች ውድድር አውደ ርዕይ መካሄድ ጀምሯል።
እስከ መጪው አርብ በሚቆየው በዚህ አውደ ርዕይ የፈጠራ ሀሳቦች ውድድር በማድረግ የላቀ ውጤት ያመጡ ተሳታፊዎች እንደሚሸለሙም ተገልጿል።
በትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና የትምህርት አመራር ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ አውደ ርዕዩ የአገርን ዕድገት የሚያሳልጡ የፈጠራ ሥራዎችን የሚያበረታታ ነው።
ሌሎች የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ዜጎች ለማበረታት እና መንገድ ለማሳየት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የፈጠራ ሀሳብ ባለቤቶች በሀገሪቱ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያሉ መልካም ዕድሎችን በመጠቀም ሀሳቦቻቸውን ወደ ተግባር መለወጥ ይገባቸዋል ብለዋል።
የስቴም ፓወር ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ስሜነው ቀስቅስ በበኩላቸው፥ ድርጅቱ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ተማሪዎች ውጤታማ እዲሆኑ የስልጠና ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት አይ ቢ ኤም ከተሰኘ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር 25 ሺህ ተማሪዎች ማሰልጠን የሚያስችል መርሃ ግብር ይፋ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ተማሪዎች የፈጠራ ሀሳባቸውን አበልጽገው ሥራ ላይ እንዲያውሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ጠቁመው የፈጠራ ባለቤቶች ዕድሉን እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል።
ከአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች መካከል ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ የመጣው ወጣት ሳሙኤል አማረ ለግብርና ሥራ የሚጠቅም ድሮን ቴክኖሎጂን በመፍጠር ለዕይታ አቅርቧል።
ድሮኑ ኬሚካሎችን ለመርጨትና ሌሎች የግብርና አገልግሎቶችን የሚሰጥ መሆኑን ገልፆ፥ የፈጠራ ሀሳቡን ከብዙ ፈተና በኋላ ወደ ውጤት መቀየሩን አስረድቷል።
ከአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች መካከል ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ የመጣው ወጣት ሳሙኤል አማረ ለግብርና ሥራ የሚጠቅም የድሮን ቴክኖሎጂን በመፍጠር ለዕይታ አቅርቧል።
የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ዜጎች በፋይናንስ በመደገፍ ለውጤት እንዲበቁ ማድረግ ይገባል ብሏል።