የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በበርካታ አመላካቾች አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በበርካታ አመላካቾች አበረታች ውጤት እያስመዘገበ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2017(ኢዜአ)፦ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው በበርካታ አመላካቾች አበረታች ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋትና ዘመናዊና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ለመመስረት፤ ፈጠራን በማበረታታት ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር፤ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሁም ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብ ካለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ገቢራዊ መደረጉ ይታወሳል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራና የቀጣይ የቤት ሥራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም፤ በፖሊሲ ማሻሻያ ትግበራው የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን፣ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር መመሪያ እንዲሻሻል፣ ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ፈቃድ መስጠት የሚያስችሉ ማሻሻያዎች ተደርገዋል ብለዋል፡፡
መንግስት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን በማከናወኑም የፖሊሲ ማሻሻያው አበረታች ውጤት እንዲያስመዘግብ አስችሎታል ነው ያሉት፡፡
ከማሻሻያው በፊት በባንክና በትይዩ ገበያ መካከል የነበረው የውጭ ምንዛሬ ልዩነት 95 ነጥብ 7 በመቶ እንደነበር ገልጸው፤ አሁን ላይ ልዩነቱን ተቀራራቢ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 152 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል፡
በመስከረም ወር በባንኮች በኩል የተላከው ሀዋላ(ሪሚታንስ) ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 69 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንም ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት የቅርብ ክትትል እንዲሁም ችግሮች ሲያጋጥሙ የሚወሰዱ ፈጣን እርምጃዎችም ለስኬቱ ቁልፍ ሚና ማበርከታቸውን አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዚህ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ባለፉት ሶስት ወራት በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በማዕድን እና ዲጅታል ዘርፍ አፈፃፀም የተመዘገበው ውጤት ትንበያውን ማሳካት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ የዋጋ ግሽበት ካለፉት ስድስት ወራት ጀምሮ በተከታታይ ቅናሽ እያሳየ መሆኑንም እንዲሁ፡፡
ለአብነትም የዋጋ ግሽበቱ ግንቦት ወር 2016 ዓ.ም ከነበረበት 23 ነጥብ 3 በመቶ በጥቅምት 2017 ዓ.ም ወደ 16 ነጥብ 1 በመቶ ዝቅ እንዲል መደረጉን አንስተዋል፡፡
ይህም መንግስት መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎችን ዋጋ ለማረጋጋት የቀየሳቸው ፖሊሲዎችና የወሰዳቸው ተከታታይ እርምጃዎች ውጤታማ መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡
ማሻሻያው ከፍተኛ የማህበራዊ ጫና ሳያደርስ ተግባራዊ ተደርጓል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ይህ ስኬት ቀጣይነት እንዲኖረው የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ ልምድን ማሳደግ ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ብሔራዊ የታክስ ሪፎርም ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራ ጀምሯል ብለዋል፡፡
የታክስ አስተዳደሩን ለማጠናከር ተጨማሪ አዳዲስ አሰራሮች እንደሚዘረጉ ገልጸው፤ የታክስ አሰባሰብ ሪፎርሙ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሶስት ወራት የተሻለ ገቢ እንዲሰበሰብ ማድረጉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
መንግስት የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ ጫና እንዳያሳድር የበጀት ድጎማ ሥርዓት ዘርግቶ ገቢራዊ ማድረግ ጀምሯል ብለዋል፡፡
ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ማስተካከያ እንዲሁም የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራምን ማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
ለነዳጅ፣ ለማዳበሪያ፣ ለዘይትና ለመድሀኒት ድጎማ የሚያስፈልገው ተጨማሪ ወጪ በፌደራል በጀት እንዲካተት መደረጉን ጠቅሰው፤ ድጎማውን ታሳቢ ያደረገ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ ማሻሻያውን ተከትሎ ኢትዮጵያ እያስመዘገበችው ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት በቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር እንዲጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡