ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዋነኛ ትኩረቶች በኮፕ 29

29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ29) ትናንት በአዘርባጃን ባኩ ከተማ ተጀምሯል።

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴን(ዶ/ር)ን ጨምሮ የኢትዮጵያ ልዑክ በጉባዔው እየተሳተፈ ይገኛል።

በጉባኤው ላይ የሀገራት መሪዎች እና ከፍተኛ ባለስልጣናት ተሳታፊ ሆነዋል።


 

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና በአካባቢ ጥበቃ እየሰራች ያለችውን ስራ የሚያሳይ መካነ ርዕይ(ፓቪሊዮን) መርቀው ከፍተዋል።

ኢትዮጵያ በጉባዔው ላይ የምታንጸባርቃቸውንና ትኩረት የምታደርግባቸውን መስኮች አስቀድማ ይፋ ማድረጓ ይታወቃል።

አረንጓዴ አሻራ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ግብ፣ የብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅዶች ትግበራ እና በአየር ንብረት ለውጥ ለሚደርስ ጉዳት እና ኪሳራ የሚከፈል የፋይናንስ ፈንድ ማዕቀፍ ኢትዮጵያ ትኩረት ከሰጠቻቸው ጉዳዮች በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።

የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን፣ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ ግብን ጨምሮ ሌሎች ያልተቋጩ ጉዳዮች እንዲፈቱም ድምጿን ታሰማለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአየር ንብረት ለውጥ ገፈት ቀማሽ የሆኑ የአፍሪካ እና በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት የጋራ አቋም በመያዝ ግፊት እንዲያደርጉ ጥረት እንደምታደርግም ተገልጿል።

በጉባኤው በእስከ አሁን ድርድሮች በእንጥልጥል ላይ የቆዩ ረቂቅ የስምምነት ሰነዶች የማጽደቅ ጉዳይ ላይ አቋሟን እንደምታንጸባርቅም ይጠበቃል።


 

ኢትዮጵያ በጉባዔው ጥቅሞቿን ለማስከበር የተቀናጀ የዲፕሎማሲ ስራ እንደምታከናወን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ኢትዮጵያ በጉባዔው የአየር ንብረት ለውጥ ግቦቿ እና የብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ እቅዶቿ ትግበራ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ለማግኘት ጥረት እንደምታደርግ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያን የኮፕ29 ተሳትፎ የሚያስተባብረው የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሀገሪቱ በጉባዔው ላይ የሚኖራትን ተሳትፎ አስመልክቶ የድርጊት መርሃ ግብር ማዘጋጀቱ ይታወቃል።

የጉባዔውን ተሳትፎ የሚያስተባብር ብሔራዊ የስትሪንግ ኮሚቴ እና በኮሚቴው ስር የተለያዩ የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል።

የኢትዮጵያን ፍላጎቶች እና ጥቅሞች የሚያስከብሩ 20 የጎንዮሽ እና 40 የሁለትዮሽ ውይይቶችን ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ከጉባዔው ጎን ለጎን የሀገራት መሪዎች እና ሚኒስትሮች የሚሳተፉባቸው የተለያዩ መድረኮች ይካሄዳሉ።

ኢትዮጵያም በጉባዔው ሶስት የአጋርነት ስምምነቶችን እንደምትፈራረምም ይጠበቃል።

ዴንማርክ፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም(ዩኤንዲፒ)፣ የተባበሩት መንግስታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ)፣ የዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ(ኢፋድ) እና ሌሎች አጋር አካላት ለኢትዮጵያ የኮፕ29 ተሳትፎ ድጋፍ እንዳደረጉም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ግቦቿን እውን የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ አጋርነቶችን የማጠናከር ስራ በ29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ29) እንደምታከናውን ተመላክቷል።

የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ(Climate Finance)፣ የውቅያኖሶችና የአየር ንብረት ለውጥ ትስስር፣ ዘላቂ እና ፍትሐዊ የአየር ንብረት ለውጥ የሽግግር ማዕቀፍ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አቅም መገንባት እና ብሔራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣሚያ እቅዶች፣ የስርዓተ ጾታ እና ማህበራዊ አካታችነት እንዲሁም ከሰው ልጅ የመቋቋም አቅም በላይ የሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ አሉታዊ ተጽዕኖዎች ዋነኛ የጉባዔው የመወያያ አጀንዳዎች ናቸው።

29ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ29) የአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶችን ለመከላከልና ለመቋቋም የሚበጁ ውሳኔዎች ይተላለፉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባዔው እስከ ሕዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም