በድሬደዋ ከተማ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ ከተማ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለጸ
ድሬደዋ፤ ህዳር 3/2017(ኢዜአ) ፡- በድሬዳዋ አስተዳደር 19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን የአስተዳደሩ ምክር ቤት አፈ- ጉባዔ ወይዘሮ ፈትህያ አደን ገለጹ።
አፈ-ጉባዔዋ ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረውን የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ፤ በዓሉ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት ዜጎች በአገር ዘላቂ ልማቶች ላይ እንዲረባረቡ እያገዘ ይገኛል ።
በተለይ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ እየተከበረ የሚገኘው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል የወል ትርክቶችን እና የጋራ ማንነትን በማነፅ በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብ አገራዊ የብልጽግና ትልሞችን ላይ ተረባርቦ ዕውን እንዲያደርግ ምቹ መደላደል መፍጠሩን ገልጸዋል።
በተለይ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማ በልጆቿ መመራት በመጀመሯ በሁሉም መስክ የብልጽግና ትልሞች በተሻለ ውጤት እንዲታጀብ ማስቻሉን በማስታወስ ።
ባለፉት አምስት ዓመታት የህዝብ ተጠቃሚነትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተቀናጀ ፍጥነት በመመለስ አርአያዊ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
ይሄም ዜጎች ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር የተገኙ ውጤቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ዘንድሮም ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል በድሬዳዋ የተገኙ የለውጥ ውጤቶች በሚያጠናክሩ ዝግጅቶችና ጉብኝቶች ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በተለይ በዓሉ ህብረ ብሔራዊ አንድነት በሚያፀኑና የጋራ ትርክቶች በሚያጎለብቱ ሲንፖዚየሞችና ህገ መንግስታዊ ዕውቀቶችን በሚያሰርፁ ዝግጅቶች ከነገ ጀምሮ እንደሚከበር ተናግረዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በአርባ ምንጭ ከተማ እንደሚከበር ቀደም ብሎ ተገልጿል።