በትግራይ ክልል የእግር ኳስ ስፖርት ዘርፍን በሳይንሳዊ መንገድ መምራት እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የእግር ኳስ ስፖርት ዘርፍን በሳይንሳዊ መንገድ መምራት እንደሚገባ ተገለጸ
መቀሌ፤ ህዳር 03/2017 (ኢዜአ)፦ በትግራይ ክልል የእግር ኳስ ስፖርትን በሳይንሳዊ መንገድ እንዲመራ በማድረግ ብቃት ያላቸው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት በየደረጃው ያሉት አሰልጣኞችን አቅም ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የ''ዲ'' ደረጃ (ላይሰንስ) አሰልጣኞች ስልጠና የማጠቃለያ መርሃ ግብር ዛሬ በመቀሌ ተካሄዷል።
በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የስፖርት ኮሚሽን የትምህርትና ስልጠና አስተባባሪ አቶ ሃፍቶም በርሄ በወቅቱ እንዳሉት፤ የክልሉን የእግር ኳስ ስፖርት ለማሻሻልና ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ስልጠናው አስፈላጊ ነው።
ለ11 ቀናት የአሰልጣኝነት ኮርስ የተከታተሉ የስፖርት ሙያተኞች የሚያሰለጥኑዋቸው ታዳጊዎች በመልካም ስነ ምግባር የታነፁ እንዲሆኑም እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ስልጠናውን ከሰጡት መካከል ኢንስትራክተር አለባቸው ተገኝ፣ስልጠናው በስነ-ልቦናና በአካል ብቃት ጠንካራ የሆነ ዜጋን ለማፍራት እንደሚያስችል ተናግረዋል።
እንዲሁም ሠልጣኞች የእግር ኳስ ጥበብን የተላበሱ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የሚያስችላቸውን ሙያዊ እውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ መደረጉን ኢንስትራክተሩ ገልፀዋል።
በተለያዩ የአገሪቷ ክልሎችም ተመሳሳይ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልፀው፤ መሰል ሥልጠናዎች ለአገሪቷ የእግር ኳስ ዕድገት የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣት ሰላማዊት ስብሀቱ ለ11 ቀናት በተሰጠው የአሰልጣኝነት ስልጠና ከተሳተፉ 60 የ''ዲ'' ደረጃ ሰልጣኞች አንዷ ነች።
እርሷ እንዳለችው፣ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች መሰረታዊ የስፖርት ክህሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ስልጠና ተከታትላለች።
እንዲሁም አቅማቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ በአካልና በአእምሮ የዳበሩ እንዲሆኑና "ለቀጣይ የስፖርት ህይወታቸው መሰረት እንዲኖራቸው ያስችላል" ብላለች።
ለአገራችን የእግር ኳስ ስፖርት ተተኪዎችን ለማፍራት አማራጭ የሚሰጥ ስልጠና ነው ያለው ደግሞ አሰልጣኝ ወጣት ምዑዝ መስፍን ነው።