ቀጥታ፡

በመዲናዋ የተከናወኑ የልማት ተግባራት አዲስ አበባን የለውጥ ማዕከል ማድረግ ያስቻሉ ናቸው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ በይቻላል መንፈስ የተከናወኑ ስኬታማ የልማት ተግባራት አዲስ አበባን የለውጥ ማዕከል ማድረጋቸውን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የመንግስት ተቋማትና የብልጽግና ፓርቲ የዕቅድ አፈፃጸም ግምገማ የምክክር መድረክ በአድዋ ድል መታሰቢያ አካሂዷል።

በዚሁ ጊዜ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ጥንካሬዎችን አንጥሮ በማውጣት ለበለጠ ተልዕኮ አስፍቶ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

በ2016 በጀት ዓመት የተመዘገቡ ውጤታማ ተግባራት ለተያዘው በጀት ዓመትም ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውሰዋል።

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶችን ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

በልማት ስራዎች የተመዘገቡ ስኬቶች እንደተጠበቁ ሆኖ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋሉ የጉቦኝነትና ሌብነት ዝንባሌዎች ማሻሻልና መለወጥ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች በዕቅድ የሚመራ የብልሹ አሰራር መከላከል ሥርዓት ማስፈን የሚጠበቅባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራር በሩብ ዓመት የሚቀረፍ ችግር አይደለም ያሉት ከንቲባዋ፤ ለዚህም በዕቅድ የተመሰረተ የድጋፍና ክትትል ስርዓት መከተል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዚህም በይቻላል መንፈስ የሚገነባው ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ መዋልና ማደርን የሚጠይቅ ቢሆንም በሌሎች መደበኛ ተግባራት ላይ ክፍተት መፈጠር እንደሌለበት አስረድተዋል። 

በመዲናዋ ሌት ከቀን በይቻላል መንፈስ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች አዲስ አበባን የኢትዮጵያ የለውጥ ማዕከል ማድረግ ያስቻሉ ናቸው ብለዋል። 

የተገኘው ውጤት በከተማ አስተዳደሩ መዋቅር ውስጥ ሌት ከቀን በትጋት እየሰሩ የሚገኙ የስራ ኃላፊዎች መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም ውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም ሥርዓትን በመከተል በዕቅድ የተያዙ ተግባራትን በጥምረትና በቅንጅት መምራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። 

በከተማ አስተዳደሩ የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት መድረክ ላይ በኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ የመሰረተ ልማት፣ በመልካም አስተዳደር፣ባለ ብዙ ዘርፍ እና ባለሁሉም ዘርፍ ተቋማት የመንግስትና የፓርቲ የዕቅድ አፈፃጸም ተግባራት ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም