በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረው እርጥበት በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ላሉ ሰብሎች አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረው እርጥበት በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ላሉ ሰብሎች አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 3/2017(ኢዜአ):- በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረው እርጥበት ዘግይተው ለተዘሩና በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ላሉ ሰብሎች አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የሚኖረውን የአየር ትንበያ አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ የአየር ሁኔታው የተለያዩ ሰብሎች የተሟላ እድገት እንዲኖራቸው ከማድረግ አንፃር ሰፊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያለው።
በመኸር ወቅት መጨረሻ ላይ ለተዘሩ እንደ ሽንብራ፣ ጓያና ለመሳሰሉት የጥራጥሬ ሰብሎች የተሟላ እድገት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድም አዎንታዊ ሚና ይጫወታል።
በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የደቡብ እና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚጠበቅም ነው ያስታወቀው።
የእርጥበቱ ሁኔታ በቦረና እና ጉጂ ዞኖች ለተዘሩ ሰብሎችና ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም አመልክቷል።
የእርጥበቱ ሁኔታ ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎችም ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ነው ትንበያው ያመለከተው።
በዚሁ ወቅት የሚገኘውን ዝናብ ውሃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ውሃን ለመሰብሰብና ለማከማቸትም መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርም ገልጿል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ወቅቱ ያልጠበቀ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር እንደሚችልም ነው ትንበያው ያስታወቀው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በመኸር ሰብል ስብሰባና ድህረ ሰብል ስብሰባ ተግባራት ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል አርሶ አደሩና የሚመለከታቸው አካላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ነው ያሳሰበው።
ገናሌ ዳዋ፣ በዋቢ ሸበሌ፣ ኦሞ ጊቤ ፤ስምጥ ሸለቆ ፣ኦጋዴን፣ በላይኛው እና መካከለኛው ባሮ አኮቦ፣ በታችኛው አባይ ተፋሰሶች ላይ ከእርጥበታማ እስከ ከፍተኛ እርጥበት እንደሚያገኙም አመልክቷል።
ይህን ሁኔታ ተከትሎም በተለይም የውሃ እጥረት ባለባቸውና በቆላማ ንዕስ ተፋሰሶች ላይ የሚገኘው እርጥበት የውሃ አቅርቦት እንዲሻሻል እንደሚያደርግም ትንበያው አስታውቋል።