ቀጥታ፡

ባንግላዴሽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ምጣኔ ሃብታዊ ትብብር ለማሳደግ ፍላጎት አላት - በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2017(ኢዜአ)፦ባንግላዴሽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የምጣኔ ሃብትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የበለጠ ማሳደግ እንደምትፈልግ በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ሲክደር ቦዲሩዛማን ተናገሩ።

አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላት ገልጸዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ ባንግላዴሽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የምጣኔ ሃብትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ግንኙነት ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት አላት ብለዋል።

ሁለቱ አገራት በትብብር ሊሰሩባቸው የሚችሉ የተለያዩ ዘርፎች እንዳሉ ገልጸው ንግድ፣ ባህል እንዲሁም ቱሪዝምን በአብነት አንስተዋል።

ባንግላዴሽ በጨርቃጨርቅ፣ በመድኃኒት ምርት፣ በቆዳ እንዲሁም በባህር ምግብ ከፍተኛ አቅም እንዳላት በማንሳት በዘርፉ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ሰፊ እድል መኖሩን አመላክተዋል።

የባንግላዴሽ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅና ሌሎች ዘርፎች ተሰማርተው እየሰሩ እንደሚገኙ በመጥቀስ በቀጣይ በፋርማሲቲዩካል፣ በጨርቃጨርቅና ቆዳ ዘርፍ ያለውን ኢንቨስትመንት ለማስፋት እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የባህል ግንኙነት በማሳደግ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም አንስተዋል።

ሁለቱ አገራት በተፈጥሮ ሃብት፣ በባህል፣ በቱሪስት መዳረሻና ሌሎች ዘርፎች ያሏቸው እምቅ መስህቦች የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክሩ ሃብቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ወደ ባንግላዴሽ ዋና ከተማ ዳካ የጀመረው በረራ የባህልናና የንግድ ልውውጥን ከማጠናከር አንጻር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።

ባንግላዴሽ የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ ጥሩ ወዳጅ እንደምትመለከት ገልጸው ይህንን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም