ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችውን የኢኮኖሚ ልማት ኢንሼቲቮች ለማሳካት የደን ልማት ቁልፍ ሚና አለው

አዳማ ፤ህዳር 3/2017 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችውን የኢኮኖሚ ልማት ኢንሼቲቮችን  ለማሳካት የደን ልማት ቁልፍ ሚና እንዳለው የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

 በኢትዮጵያ ደን ልማት አዘጋጅነት በደን ልማት ላይ ያተኮረ ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በኮንፈረንሱ መክፈቻ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር እያሱ ኤሊያስ እንደገለፁት ደን የአፈር ለምነትን ከማሳደግ ባለፈ የውሃና የአካባቢ ስነ-ምህዳር ሚዛን ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና አለው።

በተጨማሪም የደን ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋምና ዘላቂ የመሬት አጠቃቀምን ለማሳደግ እንደሚረዳም ተናግረዋል።

በዚህም ባለፉት ስድስት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብነት፣ ለውበትና ለደን ልማት የሚውሉ ችግኞች መተከላቸውን አስታውሰዋል።

የደን ልማት ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችውን የኢኮኖሚ ልማት ኢንሼቲቮች ለማሳካት ቁልፍ ሚና ያለው በመሆኑ በዚህ ዙሪያ የሚካሄዱ ጥናትና ምርምር ስራዎች መጠናከር አለባቸው ብለዋል።

የደን ልማት ስራው በጥናትና ምርምር ከተደገፈ አካባቢያዊ ስነ-ምህዳር ከመጠበቅ ባለፈ ከውጭ የሚገቡ የደን ውጤቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተሰሩ ስራዎች የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከነበረበት 17 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።

በተሰራው ስራም የግብርና ምርትና ምርታማነትን እያደገ መምጣቱን ገልጸው የደረቁ ወንዞችና ዥረቶች ውሃ መያዝ መጀመራቸው አውስተዋል።

የችግኝ ተከላው የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙና የአፈር መሸርሸር እንዲቀንስ ማስቻሉንም ጨምረው ገልጸዋል።

ለዚህም በደን ልማት ዙሪያ የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ስራዎች የተጀመረውን ስራ የበለጠ የሚያሳድጉ እንዲሆኑ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

የደን ልማት ሳይንሳዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወን የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ስራዎች ትኩረት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ደን ልማት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳመነ ዳሮታ ናቸው።

በተለይም የጥናትና ምርምር ስራዎች በገጠርና በከተማ በምን መልኩ መከናወን እንዳለባቸው፣ ለደን ልማት የሚውሉ የዛፍ ዝርያ ማሻሻል ስራ በቴክኖሎጂ መደገፍ ላይ ያተኮሩ መሆን እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ከዚህም ባለፈ የደን ጥበቃና አስተዳደርን ለማጠናከር እንዲሁም በሰደድ እሳትም ሆነ በጭፍጨፋ በደን ላይ የሚደርስ ጉዳት መቀነስ ላይ ያተኮሩ እንዲሆኑ አቶ ዳመነ አስገንዝበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም