ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን 190 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ የሰሊጥ ምርት ተሰበሰበ

መተማ፤ ህዳር 3/2017(ኢዜአ):- በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር ወቅቱ 190 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ የሰሊጥ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ደግሰው አየለ፤ የደረሰ የሰሊጥ ሰብል በንፋስ፣ በእንስሳትና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ሙሉ ለሙሉ መሰብሰቡን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በመኸሩ ወቅት በ516 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ሰሊጥ፣ ማሽላ፣ አኩሪ አተር፣ ጥጥ፣ ማሾ፣ ጤፍ፣ ዳጉሳና ሌላም የሰብል ዓይነት መልማቱን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ በሰሊጥ የለማው 190 ሺህ ሄክታር መሬት መሆኑን ጠቅሰው፤ ምርቱ ጉዳት ተጠብቆ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ጥራቱን በጠበቀ አግባብ መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።

በሰሊጥ ስብሰባውም ከ200 ሺህ በላይ የጉልበት ሰራተኞች መሳተፋቸውን አመልክተው፤ ከተሰበሰበው ሰሊጥም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።

ከሰሊጥ በተጨማሪ ሌሎች የደረሱ የሰብል ምርቶች እየተሰበሰቡ መሆኑን ጠቁመው፤ የምርት ብክነት እንዳያጋጥም በባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ መተማ ወረዳ የሽመለጋራ ቀበሌ አርሶ አደር ተስፋው አለነ በሰጡት አስተያየት፤ በሶስት ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን የሰሊጥ ምርት መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።

ይህም ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሊደርስ የሚችልን የምርት ብክነት ያስቀረላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በዚሁ ወረዳ የኮኪት ቀበሌ አርሶ አደር ኪዴ ጌጡ በበኩላቸው፤ በመኸሩ ወቅት በ4 ሄክታር መሬት ላይ ሰሊጥ በማልማት ሙሉውን በመሰብሰብ ምርቱን ወደ መጋዝን ማስገባታቸውን አስታውቀዋል።

ካለሙት መሬት ላይ ከ22 ኩንታል በላይ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸሩ ወቅት አጠቃላይ ከለማው 516 ሺህ ሄክታር መሬት ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም