የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የእርስ በርስ ትስስርን በሚያጠናክሩና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብቱ ክንውኖች ይከበራል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2017(ኢዜአ)፦ 19ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የእርስ በርስ ትስስርን በሚያጠናክሩና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብቱ ክንውኖች እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

በምክር ቤቱ የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዲሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገ-መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ባንቺይርጋ መለሰ የበዓሉን አከባበር አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "ሀገራዊ መግባባት ለኀብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚከበር ገልጸዋል።

የዘንድሮው በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባ ምንጭ ከተማ ይከበራል ብለዋል።

የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን የእርስ በርስ ትስስርን በሚያጠናክሩና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብቱ ክንውኖች እንደሚከበርም ተናግረዋል።

በዚህም ህዳር 25 የወንድማማችነት ቀን በሚል በታላቁ ሩጫ ለአብሮነት በተሰኘ እና በልዩ ልዩ ስፖርት ውድድሮች እንደሚከበር ገልጸዋል።

ህዳር 26 የአብሮነት ቀን በሚል የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ወደ አርባ ምንጭ ከተማ የሚገቡበት እና በእለቱ የንግድ ትርኢትና ባዛር እንደሚከፈት ተናግረዋል።

ህዳር 27 ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ቀን ሲሆን በክልሉ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ባህላቸውን የሚያሳዩበት የባህል ፌስቲቫል እና ስለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ልማት እና ባህሎች ሰፊ የሚድያ ሽፋን የሚያገኝበት መሆኑንም አስታውቀዋል።

ህዳር 28 የምክክር ቀን ሲሆን ሀገር አቀፍ ሲምፖዝየም እና የፌደሬሽን ምክር ቤት የሰላም ችቦ ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚያስረክብበት ቀን መሆኑንም አመላክተዋል።

ህዳር 29 የኢትዮጵያውያን ቀን በሚል የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ባህሎቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ኢትዮጵያውያን በአንድ መድረክ የሚገናኙበት ቀን መሆኑን ገልጸዋል።

በእለቱ የአደባባይ የባህል ትርኢት፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ርክክብ እና የበዓሉ ማጠቃለያ እና የቀጣይ አዘጋጅ ክልል ማሳወቅ መርሀ ግብር እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም