ቀጥታ፡

የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ስራ መጀመራቸው ተወዳዳሪ የፋይናንስ ዘርፍ እድገት እንዲኖር ያስችላል - የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮ ኃላፊዎች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች ስራ መጀመራቸው ውድድርን መሰረት ያደረገ የፋይናንስ ዘርፍ እድገት እንዲኖር እንደሚያደርግ የግል ምንዛሬ ቢሮ ኃላፊዎች ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ አገልግሎትና ተደራሽነትን ለማስፋት እንዲሁም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማዳበር ባወጣው መመሪያ መሰረት አስፈላጊውን መስፈርት ላሟሉ አምስት ባንክ ላልሆኑ የግል ምንዛሬ ቢሮዎች ፈቃድ መስጠቱ ይታወሳል።

የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች በሙሉ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ሀገር ጥሬ ገንዘቦችን በመግዛትና በመሸጥ እንዲሁም ከባንኮች ጋር በመቀናጀት ለወጪና ገቢ ንግድ የሚውል የውጭ ምንዛሬ በማመቻቸት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ገበያ ለማስፋትና ለማዳበር የሚረዳ ሚና እንዳላቸው በመመሪያው ተመላክቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮ ኃላፊዎች፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በፋይናንስ ዘርፉ የተደረገው ለውጥ የውጭ ምንዛሬ ግኝት አማራጭን ለማስፋት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮ ፎሬክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤፍሬም ተስፋዬ፤ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ በውድድር ላይ የተመሰረተ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የውጭ ምንዛሬ አገልግሎትና ተደራሽነትን ለማስፋት ይዞ የመጣውን እድል በመጠቀም ወደ ዘርፉ መግባታቸውን ነው የገለጹት፡፡

የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ያለ ጉምሩክ ዴክላራሲዮን ከደንበኞች እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፣ የጉምሩክ ፈቃድ በማቅረብ ደግሞ ከዚያ በላይ የውጭ ምንዛሬ በጥሬ ገንዘብ መግዛት እንደሚችሉ በመመሪያው ተቀምጧል፡፡

በተመሳሳይ ተፈላጊ የጉዞ መረጃ ላላቸው የግል ተጓዦች እስከ 5 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ ለንግድ ሥራ ተጓዦች ደግሞ እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በጥሬ ገንዘብ መሸጥ እንደሚችሉም ነው ብሔራዊ ባንክ የገለጸው።

በዚህ መሰረት በቀን ከ10 እስከ 15 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እየገዙና እየሸጡ እንደሚገኙ በማስረዳት በቀጣይም አገልግሎቱን አስፍተው እንደሚሰጡ ገልጸዋል።


 

ሌላኛው የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ስራ የገባው የሮበስት ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጌቱ ሙሊሳ በበኩላቸው የግል ምንዛሬ ቢሮዎች በዘላቂነት ህጋዊነትን ለማስፈን አጋዥ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በውድድር ላይ የተመሰረተ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት ለግል ዘርፉ ይዞ የመጣውን እድል በመጠቀም ዘርፉን መቀላቀላቸውንም አስታውሰዋል።

የግል ምንዛሬ ቢሮዎች መከፈታቸው አማራጭ የውጭ ምንዛሬ ግብይትን በማስፋት የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ባንክ ያልሆኑ ምንዛሬ ቢሮዎች የጥቁር ገበያ ልዩነትን በማጥበብና አማራጮችን በማስፋት በሂደት ጥቁር ገበያውን ለማክሰም እንደሚያግዙም ነው የገለጹት፡፡

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ተከትሎ በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት 80 በመቶ መጨመሩን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የማሻሻያውን የሶስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት አስመልክተው ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም