የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራን ገመገመ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2017 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብሰባው ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ያለበትን ደረጃ በጥልቀት ገምግሟል፡፡

በግምገማው በዋናነት ትኩረት ያደረገው የልማት ተነሺዎች የተስተናገዱበትን አግባብ፤ በመንግስት የሚኖሩ የነበሩ የተነሱበት አግባብ፤ መሰረተ ልማት የተሟሉላቸው መሆኑን፤ በተመሳሳይ ሁኔታ የግል ተነሺዎች ደግሞ የካሳ የ3 አመት የቤት ኪራይ እና ምትክ መሬት መውሰዳቸውን ፤የትራንስፖርት አቅርቦት እና የሞራል ካሳ በህጉ መሰረት የተከፈለ መሆኑን የተተነተነ ሪፖርት በየኮሪደሩ አስተባባሪዎች ቀርቦ መገምገሙ ተገልጿል።

በግምገማውም ሁሉም ህጋዊ ውል ወይም ሰነድ ኑሯቸው እንዲሁም በመጠለያ በተገኙበት ተጠልለው የሚኖሩ ነዋሪዎችን ሁሉ የቤት መስተንግዶ እና የቤት መሰረተ ልማቶች በተሟላላቸው እጅግ የተሻለ ፣ ንፁህ ፣ መሠረታዊ መገልገያዎች የተሟሉላቸው ቤቶች የተስተናገዱ መሆኑን፤ ለመኖሪያ ምቹ አካባቢ ያገኙ ስለመሆኑ እና አንዳንድ ሳይቶች ላይ የመንገድ ደረጃውን ለማሻሻል ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ሪፖርት ቀርቦ ካቢኔው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ውሳኔ ማሳለፉም ተመላክቷል።


 

ሌሎች ሳይት ላይ አስፈልጊው መሰረተ ልማት ተጠናቆ ነዋሪዎች የየእለት ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉም ተጠቅሷል።

የማህበራዊ ኑሯቸው ሳይበታተን እድር ፤ ማህበር እና አብሮነታቸው የመሰረቱት ማህበራዊ መስተጋብር እንደተጠበቀ መስተናገዳቸውና አቃቂ ፤ገላን ጉራ ፤ፉሪ ሃና ፤አራብሳ አምስት እና ስድስት አያት ሶስት፤ ላፍቶ ሃይሌ ጋርመንት እና ለሚኩራ አጠገብ የተሰሩት ሎኮስት አየር ጤና፣ ቂርቆስ ለገሃር አካባቢ ፤አራዳ ሰባ ደረጃ አካባቢ በማሃል ከተማ የተገነቡ ቤቶች ላይም መስተናገዳቸውን እና አፈፃፀሙም ጥሩ መሆኑን ካቢኔው መገምገሙ ተገልጿል።

የመሠረተ ልማት ቅንጅት አካላት ከከተማ እስከ ፌደራል ተቋማት የነበራቸው ተሳትፎ በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ካቢኔው በጥንካሬ መገምገሙም ተመላክቷል።

በተጨማሪም መሬት እና ካሳ ምትክ እስካሁን ድረስ ብቻ ከ4.6ቢሊየን ብር በላይ መከፈሉንና የሁለት አመት የቤት ኪራይ መከፈሉን እንዲሁም ቀሪ ተነሺዎችም ቅድመ ዝግጅት ሂደት ካቢኔው በጥንካሬ መገምገሙ ተገልጿል ።

በሌላ በኩል በኮሙኒኬሽን ሥራዎች በደንብ ደጋግሞ ለሕዝብ መረጃን ማድረስ ላይ ከዚህ በላይ ማድረስ እና ተደጋጋሚ የሚዲያ ሽፋን ያላቸው የመረጃ ስርጭት ለህብረተሰቡ መድረስ እንዳለበት ካቢኔው ማሳሰቡም ተጠቅሷል።

መረጃን የሚያዛቡ እና ሀገር እንዳትለማ ውዥንብር በሚፈጥሩ የተለያዩ ዝንባሌዎች የሚያሳዩ የመረጃ ምንጮችን እና አካላት ላይ ህጋዊ ርምጃ መወሰድ እንዳለበት በአፅንኦት መነሳቱም እንዲሁ::

በ2ኛው ዙር ኮሪደር ልማት ስራ 2879 ሄክታር ስፋት ፤ 135 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ርዝመት ያለው ሲሆን ፤ 240 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ 237 የእግረኛ መንገድ ፣ 32 የህፃናት መጫዎች ቦታዎች ፣ 79 የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች ፣ 114የታክሲ እና አውቶቡስ መጫኛ እና ማውረጃ ፣ 58 የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎች፣ 368 ሄክታር አረንጋዴ ልማት ሽፋን ያላቸው ቦታዎች፣ የ 111 ኪ.ሜ ሳይክል መንገድ ፣ 17 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ 106 የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ 121 ኪ.ሜ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ፣ 182 ኪ.ሜ ድሬኔጅ መውረጃ መስመር ፣ 50 የተሸርካሪና እግረኛ መተላለፊያ ፣ 75 ኪ .ሜ ሪቴይኒንግ (የድጋፍ ግንብ) ስራዎችን የሚያካትት ነው ተብሏል ::

የዚህን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ክትትል ማሳደግ፤ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ የተተገበሩ የአንደኛ ዙር ኮሪደር ልማት ልምዶች ተቀምረው ለሁለተኛው ዙር በተሻለ ብቃት መስራት እንደሚያስፈልግ፤ ቅንጅታዊ አሰራርም በተጠናከረ መልኩ አሳድጎ አሁን ካለው በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ካቢኔው ማሳሰቡን የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም