በሩብ ዓመቱ የአእምሯዊ ንብረት መስፈርቶችን ላሟሉ ከ1 ሺህ 300 በላይ ጥያቄዎች የፈቃድ ማረጋገጫ ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በሩብ ዓመቱ የአእምሯዊ ንብረት መስፈርቶችን ላሟሉ ከ1 ሺህ 300 በላይ ጥያቄዎች የፈቃድ ማረጋገጫ ተሰጥቷል
አዲስ አበባ፤ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦በሩብ ዓመቱ የአእምሯዊ ንብረት መስፈርቶችን ላሟሉ ከ1 ሺህ 300 በላይ ጥያቄዎች የፈቃድ ማረጋገጫ መስጠቱን የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የአእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የአእምሯዊ ንብረት ምንነት፣አስፈላጊነትና የጥበቃ ስርዓትን በሚመለከት ከክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማትና ኤጀንሲዎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
ስልጠናው የአእምሯዊ ንብረት ምዝገባና ጥበቃ ግንዛቤን በማሳደግ በተደራጀና በተናበበ መልኩ በትብብር ለመስራት ዓላማ ያደረገ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በአእምሯዊ ንብረት ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ኤሊያስ ሙሀመድ ባለስልጣኑ የንግድ ምልክት፣የፈጠራ ባለቤትና የቅጅና ተዛማጅ መብቶች እንዲጠበቁ ይሰራል ብለዋል፡፡
በዚህም የአሰራር ማሻሻያ በማድረግና የቴክኖሎጂ አሰራር በመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የፈጠራ ስራና የንግድ ምልክት ምዝገባና ጥበቃ መደረጉ የፈጠራ ባለቤቶች ተወዳዳሪና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያበረታታ እንደሆነ አስረድተዋል።
በዚህም በሩብ ዓመቱ በንግድ ምልክት፣በፓተንት፣የቅጅና ተዛማጅ መብቶች መስፈርት ላሟሉ ከ1 ሺህ 300 በላይ ጥያቄዎች የፈቃድ ማረጋገጫ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ሳምራዊት ብርሃኔና ያቆብ ማሞ ስልጠናው ባለድርሻ ተቋማት ተቀራርበው እንዲሰሩ ምቹ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
መሰል ስልጠናዎች በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡