በኮሙኒኬሽን ተቋማትና የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሮች የሚከናወኑ የተግባቦት ስራዎች ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚያስገነዝቡ መሆን ይገባቸዋል - ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በኮሙኒኬሽን ተቋማትና የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሮች የሚከናወኑ የተግባቦት ስራዎች ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚያስገነዝቡ መሆን ይገባቸዋል - ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2017(ኢዜአ):- በኮሙኒኬሽን ተቋማትና የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሮች የሚከናወኑ የተግባቦት ስራዎች ዓላማ ተኮር እና ብሔራዊ ጥቅሞችን የሚያስገነዝቡ መሆን እንዳለባቸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሀገራዊ የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች አፈጻጸምን ገምግሟል።
በበይነ መረብ በተካሄደው የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ የክልል እና ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ተቋማት እና የፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።
የአገልግሎቱ፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ተቋማት እና የፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ክፍሎች የሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸሞች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ በተናበበ እና በተቀናጀ የጋራ ዕቅድ በመመራት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና የሕዝብን የመረጃ ፍላጎት የሚያሟሉ መረጃዎች ተደራሽ መደረጋቸው፣ ኹነቶችና የንቅናቄ አጀንዳዎች በተቀናጀ መልዕክትና የሚዲያ ስምሪት መመራታቸው በጥንካሬ ተነስተዋል።
ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ጥሩ መናበብ የታየበትና ወጥ ሀገራዊ የኮሙኒኬሽን ሪፖርት ማቅረብ የተጀመረበት መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ይህን ለማጠናከር የበለጠ ቅንጅትና ተናባቢነት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
የተግባቦት ሥራዎች ዓላማ ተኮር እና ሀገራዊ ትልሞችን የሚያስገነዝቡ መሆን እንደሚገባቸው ያሳሰቡት ሚኒስትሩ በቀጣይ የምንሠራቸው የተግባቦት ሥራዎች የመንግሥትንና የሀገርን ትልሞች የሚያስገነዝቡ፣ የተሳሳቱና ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያርሙ፣ የሕዝብን የመረጃ ፍላጎት የሚመልሱ እና ሁሉንም የሚዲያ አማራጮች የሚጠቀሙ መሆን አለባቸው ብለዋል።
በውጤቱም የሕዝብንና የመንግሥትን ትምምን ማጠናከር፣ የሀገር እና የመንግሥትን ገጽታ መገንባት እንዳለባቸው መግለጻቸውን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
በተለይ በሀገር ላይ የሚቃጡ አሉታዊ እና የተቀናጁ ሐሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ ሀገራዊ ሕልሞችን ለማሳካት ምልዓተ ሕዝቡን የሚያነሳሱ መረጃዎችን በየጊዜው በመስጠት የሚዲያ አጀንዳ ብልጫ መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የተግባቦት ሥራው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ሪፎርሞችን እንዲሁም ማኅበራዊና ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን በተጨባጭ ማስገንዘብ ላይ ማተኮር እንዳለበትም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የክልል እና የከተማ አስተዳደር የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች እና የፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች የዘርፉ አደረጃጀት እና መዋቅር እየተጠናከረ የተግባቦት ስራው እንዲጎለብት አገልግሎቱ ድጋፍና ክትትሉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የመንግሥት መረጃ ተደራሽነትን በመምራት፣ የተናበበና የተቀናጀ ተግባቦትን በማጎልበት የሀገርና የመንግሥት ገጽታን የመገንባት ሚናን እንዲወጣ በደንብ ቍጥር 488/2014 መቋቋሙን የአገልግሎቱ መረጃ ያመለክታል።