የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲንጋፖር ዜጎች የኢትዮጵያን ድንቅ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚጎበኙበትን እድል ፈጥሯል - የሲንጋፖር የጉዞና ጭነት አገልግሎት ወኪሎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲንጋፖር ዜጎች የኢትዮጵያን ድንቅ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚጎበኙበትን እድል ፈጥሯል - የሲንጋፖር የጉዞና ጭነት አገልግሎት ወኪሎች
አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈጣን እድገት የሲንጋፖር ዜጎች የኢትዮጵያን ድንቅ የቱሪስት መዳረሻዎች የሚጎበኙበትን እድል መፍጠሩን የሲንጋፖር የጉዞና ጭነት አገልግሎት ወኪሎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሲንጋፖር ለሀገሪቱ ለተጓዦች፣ የጉዞና የጭነት አገልግሎት ወኪሎች የማበረታቻ ሽልማት መስጠቱ ይታወቃል፡፡
ኢነርጂያ፣ ሲንጋፖር ፖስት ኃ/የተ/የግ/ ማህበር፣ ኤርሰርቭ ግሩፕ፣ ሲቲስቴት ትራቭል፣ እና ኤር ፍራይት ሲንጋፖር እውቅና የተሰጣቸው ተቋማት ናቸው፡፡
የሲቲስቴት ተራቭል ዋና ዳይሬክተር አልበርቶ ሆ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሲንጋፖር ያዘጋጀው ሁነት አየር መንገዱ ምን ያህል ታላቅና እንዴት ውጤታማ እንደሆነ አስረድቶኛል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከሲንጋፖር ለማስተሳሰር የሚያደርገው አስደናቂ እንቅስቃሴ አድናቆት የሚቸረው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሲንጋፖር የቱሪዝም አጋሮች ጋር በመተባበር የሲንጋፖርን ማህበረሰብ ማሳተፍና ከንግድ ባለፈ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሥፍራዎች እንዲጎበኙ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
በሲንጋፖር የኢትዮጵያ ተወካዮች በገበያ እና ከጎዞ ወኪሎች ጋር በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸው፤ ይሄውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጋራ የጉዞ ፓኬጅ ማዘጋጀት ይችላል ብለዋል፡፡
የሲንጋፖር ኤር ፍራይት ዳይሬክተር ካሪል ፋን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባዘጋጀው መርሀ ግብር ላይ ኢትዮጵያ ምን ያህል ማራኪ አገር እንደሆነች አይቻለሁ፤ ለመጎብኘትም ጓጉቻለሁ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ እና ሲንጋፖር መካከል ትስስር በመፍጠር የሚያደርገውን ግስጋሴም አድንቃለሁ፤ የባህል ትብብርን ያሳድጋልም ብለዋል፡፡
አየር መንገዱ በአፍሪካ ትልቁና በፍጠነት እያደገ ያለ መሆኑን ገልጸው፤ የጭነት ፍላጎቶችን በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኤርሰርቪስ ግሩፕ ኮሜርቪያል ማናጀር ክሎኤ ሊም፤ አየርን መንገዱ ከአስር ምርጥ የጎዞ ወኪሎች ይመድበናል ብለን አልጠበቅንም ነበር ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ A350-1000 በቅርቡ ማስገባቱ የአየር መንገዱን አቅም የሚጨምር፤ ለተለያዩ ወደ ኢትዮጵያና አፍሪካ እንዲሁም ሌሎች አህጉራት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሲንጋፖር ፖስት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ ቪስነሽ ናጋራጃን፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከኤዥያ በማገናኘት የጎላ አበርክቶ አለው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እምቅ አቅም ያለው ተቋም መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ትብብራችንን የበለጠ ማጠናከር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
የሲንጋፖር የጉዞና የጭነት አገልግሎት ወኪሎች፤ የአየር መንገዱ የሰፋ መዳረሻ በተለይ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ወቅት ደንበኞችን ወደ መነሻ ስፍራ መውሰድ ያስችላል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ የሲንጋፖር፣ አውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ ቀጣናዊ ሥራ አስኪያጅ ተሊላ ደረሳ፤ የጉዞ ወኪሎቹ ዘመናዊ የጎዞና የካርጎ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ፤ ለቱሪዝም፣ ለማህባረዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ወሳኝ የሚነ እንደሚጫወቱ ገልጸዋል፡፡
የሲንጋፖር መስመር በኤዥያ አህጉር ካሉ ምርጥ እና አትራፊ የንግድ መስመሮች አንደኛው መሆኑን ገልጸው፤ ያለ አጋሮቻችን ትብብር ይሄን ማሳካት አይቻለም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካና ኤዥያ መካከል ኢኮኖሚ ትብብር፣ ንግድ፣ እና የባህል ልውውጥን ለማሳደግ እንደመሳሪየ ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡